ወንድም ሳላህ
ከታላላቅ የአሏህ [ﷻ] ነቢያት መካከል አንዱ የሆነው ኢየሱስ ሰው፣ ባሪያ፣ ነቢይ እና መልዕክተኛ ብቻ መሆኑ በማያሻማ መልኩ በቁርኣን ውስጥ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ከዚህ የዘለለ ቅንጣት ያኽል ስልጣን እንዳሌለው እና ለእርሱም እንደማይገባው በራሱ አንደበት መናገሩን ጌታ አምላካችን ገልጿል፣ (ሱራ 5፥116)። በእስልምና አምልኮ የሚገባው ለአንዱ አምላክ ለአሏህ ብቻ ሲሆን ከእርሱ ውጪ ሌላን አካል መገዛትም ሆነ ለእርሱ አጋር ማድረግ ሺርክ መሆኑ የመጀመሪያው አንቀጸ-ዕምነት ነው። ኢየሱስ አምልኮ የማይገባው ባሪያ መሆኑንና ይህን ባርነቱንም ፈጽሞ እንደማይጠየፍ በግልጽ ተቀምጧል፣ (ሱራ 7፥172)። ይህን እወነታ መቀበል የከበዳቸው አንዳንድ ሙስሊም ያልሆኑ አካላት የቁርኣኑን አንቀጽ ከዐውድ በማጋጨት፣ የቋንቋውን ሰዋሰው በሚንድ መልኩ ከታች የሚገኘውን አንቀጽ ለኢየሱስ አምላክነት ለመጥቀስ ይሞክራሉ:-
اتَّخَذُوا أَحْبَارَهُمْ وَرُهْبَانَهُمْ أَرْبَابًا مِّن دُونِ اللَّهِ وَالْمَسِيحَ ابْنَ مَرْيَمَ وَمَا أُمِرُوا إِلَّا لِيَعْبُدُوا إِلَٰهًا وَاحِدًا لَّا إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ سُبْحَانَهُ عَمَّا يُشْرِكُونَ
ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለውን አንድን አምላክ ሊገዙ እንጂ ያልታዘዙ ሲኾኑ ሊቃውንቶቻቸውንና መነኮሳታቸውን፣ የመርየምን ልጅ አልመሲሕንም ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው ያዙ፡፡ ከሚያጋሩት ሁሉ የጠራ ነው፡፡ (📗Qur’an 9:31)
እንደው አሁን ሌላ አንቀጽ ጠፍቶ ነው በግልጽ ኢየሱስን አታምልኩት የሚለውን አንቀጽ ጠምዝዛችሁ ‟ኢየሱስ አምላክ ነው” ብሏል የምትሉን ? ትንሽ ለሕሊናችሁ አይከብድም ተወዳጆች ? አንቀጹን ግን አስተውላችሁታል ? እስኪ በደንብ ተመልከቱ ! ከጅምሩ እንዲህ ይላል ‟ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለውን አንድን አምላክ ሊገዙ እንጂ ያልታዘዙ ሲኾኑ…” እርሱ የሚለው ነጠላ ተውላጠ ስም (Pronoun) የሚገልጸው አንድን ማንነት ብቻ ነው። አላህ እና ኢየሱስ ደግሞ ሁለት ማንነቶች ናቸው። አንቀጹ እያስተማረ ያለው እኮ ‟እርሱ ተብሎ የተገለጸውን አንድን አምላክ ብቻ እንዲያመልኩ መታዘዛቸውን ነው” አንቀጹ «እርሱ» እያለ አላህንና ኢየሱስን ነው የሚለው ማለት ከቋንቋ ሕግ ጋር መጋጨት አይደለምን ?
ከመሰረቱ ይህ ሙግት ዐውድንም ሆነ፣ ሰዋሰውን፣ ታሪክንም ሆነ የትኛውንም የስነ-አፈታት ጥናት መሰረት ያደረገ አይደለም። እስኪ በቋንቋው ሕግ ይህ ሙግት ውድቅ መሆኑን እንመልከት:-
በአንቀጹ ላይ ‟አህባረሁም” أَحْبَارَهُمْ የሚለው ሦስተኛው መደብ-ተውላጠ ስም ሙያው “መንሱብ” مَنْصُوب ማለትም «ተሳቢ» “Accusatives case” መሆኑን አንባቢ ልብ ይሏል። በተመሳሳይ ‟ሩህባነሁም” وَرُهْبَانَهُمْ የሚለው ሦስተኛው መደበ-ተውላጠ ስምም ልክ እንደ ቅድሙ መንሱብ ‟Accusative” ተሳቢ ሙያ መሆኑን ልብ በሉ። ‟አርባባን” أَرْبَابًا የሚለውም ቢሆን በፈትሃ «¯» የተቀመጠ ተሳቢ ሙያ ነው። በጣም ጥሩ ! አሁን ደግሞ ቀጣዩን እንመልከት:- ከአርባብ ቡኋለ ቀጥሎ የመጣው ስም የአላህ ነው። ‟አላህ” اللهِ የሚለው ስም በተለያ ቅርፅ (ሙያ) “መጅሩር” مَجْرُور ማለትም አገናዛቢ “genetive case” ሆኖ እናገኘዋለን።
ከአላህ ቡኋለ የመጣው ስም ደግሞ የኢየሱስ ነው፣ አሁን በደንብ ልብ በሉ ‟ወል መሲሀ” وَالْمَسِيحَ የሚለው ስም ልክ እንደ አህባር እና ሩህባን ሁሉ መንሱብ “Accusative Case” ሆኖ ነው የተቀመጠው። በፍጹም በአገናዛቢ ሙያ (genetive) አይነበብም። ስለዚህ ዷሚሩ ኢየሱስን ከአላህ ጋር ሳይሆን ከሊቃውንቶች እና መነኮሳት ጋር ይመድበዋል። ይህ የቋንቋውን ሰዋሰው መሰረት ያደረገ አፈታት ነው፣ ነገሩ ዐረብኛ እስከሆነ ድረስ መታየት ያለበት የቋንቋው ሕግ ነው። የቋንቋው ሕግ ደግሞ ኢዕራብ አለው፣ ይህ ኢዕራብ “Case” በተሽኪሎች ይለያል። የፈለገ ያህል ዋው ‟و” በመካከላቸው ብትገባ ሁሌም “እና” ተብሎ ይተረጎማል ማለት አይደለም።
መቼም ይህንን ሙግት የሚያነሱት ሰዎች በቋንቋ ላይ ቅንጣት ታክል እውቀት እንዳሌላቸው እሙን ነው። ሙግታቸውም ቋንቋው ላይ መረዳት ከሌላቸው ዐረብ ተናጋሪ ክርስቲያኖች የተኮረጀ እንደሆነ ይታወቃል። ታድያስ ይህንን የሰዋስው ሙግት ስናቀርብ በተመሳሳይ Argument ማስተባበል ስለማይችሉ አንድ የሚናገሯት ማምታቻ አለች እሷም ‟የድሮ ቁርኣኖች ላይ አናባቢዎች ስለማይገኙ ይህ ሙግት ትክክል አይደለም፣ እንደውም ቀደምት ሙስሊሞች ይህን ጥቅስ ሲያነቡ ኢየሱስ አምላክ ነው ይሉ ነበር” ይሉናል ! አለማወቅ ወንጀል ቢሆን ኖሮ በሀገራችን ውስጥ አንድ ሰባኪ ከቂሊንጦ ባለመለጠ ነበር። ለማንኛውም ይህ ማምታቻቸው ውሃ የማያነሳ መሆኑን በቀላሉ ማየት እንችላለን:-
የመጀመሪያው:- የድሮ የቁርኣን እደ-ክታባት “Manuscripts” ላይ ተሽኪሎች (አናባቢዎች) አልተጻፉም ማለት በዚያን ጊዜ ሰዎች ያለ አናባቢ ያነበንቡ ነበር ማለት አይደለም። አናባቢዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ በቁርኣን ላይ የጻፉት የአረብኛ ቋንቋ የሰዋስው አባት ተብለው የሚታወቁት አቡል አስወድ አድ-ዱዐሊ ናቸው። የጻፉበትም ምክንያት በአንድ ሌሊት ከሴት ልጃቸው ጋር በሚቀመጡበት ጊዜ ልጃቸው ወደ ሰማይ እያየች በአፈጣጠሩ ትደነቅና አድናቆቷን ለመግለጽ ‟ማ አህሰኑ ሰማዕ” ما أحْسَنُ السَّماءِ ትላለች እሷ በተናገረችው አነጋገር ግን አድናቆት አይገልጽም ምክንያቱም እሷ ያለችው ‟ከሰማይ ውስጥ ምኗ ያምራል?” የሚል ትርጉም ነው የሚሰጠን። ከዚያም ይህንን የሰሙት አባቷ “ልጄ ሆይ አድናቆት እንዲህ አይገልጽም” ብለው አንዲህ እንድትል ነገሯት ‟ማ አህሰነ ሰማዕ” “ما أحْسَنَ السَّماء ይህ ማለትም ‟ሰማይ እንዴት የተዋበች ናት“ እንደማለት ነው። ከዚያ ቡኋለ ነበር ይህ የሰዋስው አባት መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ አናባቢዎችን በቁርኣን ላይ ለማስገባት ከኸሊፋው ፍቃድ ጠይቀው ሥራ የጀመሩት። ከታሪኩ እንደምንረዳው ነጥቦች በጹሑፍ ከመስፈራቸው በፊትም እንኳ በተሽኪሎች ላይ ጥንቃቄ ሲያደርጉ እንደነበር ነው። ሌላው ይቅርና የነቢዩ ደቀመዛሙርት እንኳ ሱረቱል ሮምን ሲያነቡ በተለያዩ አናባቢዎች ነው (Sunan Abi Dawud 3978 Book 32, Hadith 10) እንግዲህ ይህ አናባቢዎች ከመጻፋቸው (በጹሑፍ ከመስፈራቸው) በፊት የነበረ ታሪክ ነው። ተሽኪሎች ያኔ አልተጻፉም ማለት ድሮ ያለ ተሽኪል ይነበነብ ነበር ማለትን አያሲዝም።
ሁለተኛ:- ጥንታዊያን ሙስሊም ሊቃውንት ይህንን አንቀጽ የሚፈቱት በሚከተለው መንገድ ነው:-
وأما قوله: والمسيح ابن مريم فإن معناه: اتخذوا أحبارهم ورهبانهم والمسيحَ ابن مريم أربابًا من دون الله.وأما قوله وما أمروا إلا ليعبدوا إلهًا واحدًا، فإنه يعني به: وما أمر هؤلاء اليهود والنصارى الذين اتخذوا الأحبارَ والرهبان والمسيحَ أربابًا، إلا أن يعبدوا معبودًا واحدًا
አቡል በኽታሪይ ከ ሑዘይፋ ተቀብሎ እንዳስተላለፈው “ወልመሲሀ ኢብኑ መርየም” ሲል ትርጉሙ:- ሊቃውንቶቻቸውንና መነኮሳታቸውን፣ የመርየምን ልጅ አልመሲሕንም ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው ያዙ ማለት ነው። «ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለውን አንድን አምላክ ሊገዙ እንጂ ያልታዘዙ ሲሆኑ» ሲል ደግሞ እነዚያ አይሁዳውያን እና ክርስቲያኖች የታዘዙት አንዱን አምላክ እንዲገዙ ሲሆን እነርሱ ግን ሊቃውንቶቻቸውንና መነኮሳታቸውን፣ የመርየምን ልጅ አልመሲሕንም ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው ያዙ።
(📗ተፍሲር አጥ-ጠበሪ ቅፅ 14 ፣ ገፅ 213)
የጠያቂዎቹ ትልቁ ችግር የቋንቋውን አሰካክ እና አገባብ ባለማወቃቸው ‟ዋው” و ሁሌም አያያዥ መስተጻምር “Coordinate conjunction” ናት ብለው ያስባሉ። ይህ ደግሞ ቁርኣንን ሙሉበሙሉ እንደማያውቁት ያሳብቅባቸዋል፣ ምክንያቱም በአረብኛ ቋንቋ ሆነ በቁርኣን ውስጥ “ዋው” ሁሌም አያያዥ አይደለችምና። እስኪ የተወሰኑት ምሳሌዎችን ከቁርኣን እንመልከት:-
إِذَا جَاءَ نَصْرُ اللَّهِ وَالْفَتْحُ
የአላህ እርዳታና (መካን) መክፈት በመጣ ጊዜ [📚Qur’an 110:1]
በዚህ አንቀጽ ላይ በአላህ እና ፈትሕ መካከል ‟ዋው” ስለመጣች ‟የአላህ እና የፍትሕ እርዳታ በመጣ ጊዜ” ተብሎ አይነበብም ጭራሽ ትርጉምም አይሰጥም። ‟አላህ” اللَّهِ የሚለው ስም በአገናዛቢ ሙያ “Genetive case” ሲመጣ ፈትሕ ደግሞ በባለቤት ሙያ “Nominative” ነው የተቀመጠው፣ ስለዚህ ዶሚሩ ፈትሕን (መከፈትን) ከአላህ ጋር ሳይሆን ወደ እርዳታ (ነስር) ያስጠገዋል። እዚህ ጋር ዋው (و) ብትኖርም እንዳላያየዘችው አንባቢ ልብ ይሏል።
ስናጠቃልል:- ኢየሱስ መጽሐፍንና ጥበብን፣ ነቢይነትም የተሰጣ ባሪያ ነው (19:30) ነቢይነትን ጥበብንና መጽሐፍን የተሰጣ ነቢይ ደግሞ ከአላህ ሌላ አምላክ ነኝ ብሎ መናገር ተገቢው አይደለም (3:79) ኢየሱስ ክርስቶስ ልክ እንዳለፉት እርሱም ያለፈ የሆነ መልዕክተኛ እንጂ ሌላ አይደለም (5:75) ያለፉት መልዕክተኞች ለአምላካቸው ፍጹም የሚታዘዙ ሌተ-ቀን እርሱን ብቻ የሚያመልኩት አገልጋዮች ነበሩ። ኢየሱስም በምድር ቆይተው ለጌታው ባሪያ የሆነ ባርነቱንም በፍጹም የማይጠየፍ ነቢይ ነበር (4:172) ነቢይ ደግሞ በፍጹም አምላክ ሊሆን አይቻለውም። ኢየሱስ በቁርኣንም ሆነ ባይብል የሚያመልከው አምላክ አለው፣ ያ አምላክ ፍጹም አንድ የሆነ መለኮት ነው። ኢየሱስ ደግሞ የዚያ አምላክ አገልጋይና መልዕክተኛ ነበር (ዮሐንስ 17:3) መጽሐፍት በአንድ ድምፅ የሚመሰክሩት እውነታ ይህ ነውና ክርስቲያኖች ባሪያን አምላክ ለማድረግ ከምትጋጋጡ ሕይወት አጭር ናትና ወደ ትክክለኛ አምላክ እንድትመጡ በድጋሚ ጥሪ አቀርብላችኃለው።
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


