ወንድም ሳላህ
”…وَمَا أَدْرِي مَا يُفْعَلُ بِي وَلَا بِكُمْ إِنْ أَتَّبِعُ إِلَّا مَا يُوحَىٰ إِلَيَّ…
«…በእኔም በእናንተም ምን እንደሚሰራ አላውቅም፡ ወደእኔ የሚወረደውን እንጅ ሌላን አልከተልም…» (ሱረቱል አሕቃፍ 46፥9)
ብዙ ጊዜ ሙስሊም ያልሆኑ አካላት ከላይ ያለውን የቁርኣን አንቀጽ በመጥቀስ “ነቢዩ ሙሐመድ የራሱንም ሆነ የእናንተን የወደፊት እጣፋንታ አያውቁም ነበር፣ ገሀነም ይሁን ገነት የት እንደሚገባ እርግጠኛ አይደለም፣ ስለዚህ ለገዛ ሕይወቱ እንኳ ዋስትና ያሌላውን ሰው አንከተልም” ብለው ሲናገሩ ይደመጣሉ። ጥያቄው እስልምናን በማያውቁ ክርስቲያን ወገኖች የተነሳ ቢሆንም አሁን ላይ አንቀጹን በማጣመም ብዙዎች ህዝበ ሙስሊሙን ለማወናበድ ይጠቀሙበታል። እስኪ ቀጥታ ወደ ምላሹ እንግባ:- ወደ ትክክለኛው የቁርኣኑ ትርጉም ከመሄዳችን በፊት ነቢዩ ሙሐመድ አስቀድመው ጀነት መግባታቸውን እንደሚያውቁ እና ተከታዮቻቸውም ጭምር ጀነት መግባታቸውን እንደተናገሩ፣ ከወዲሁ የጀነት መሆናቸውን የመሰከሩላቸው ሰዎች መኖራቸውን በማሳየት ሙግቱን ከስር መሰረቱ እናፍርሰው።
1- የአላህ መልዕክተኛ ከሰው ልጆች ሁሉ በፊት ጀነት መግባታቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ገልጸዋል (ይህም የራሳቸውን እጣፋንታ አያውቁም ነበር የሚለውን ክስ ድባቅ የሚመታ ነው)
وأنا سيِّدُ الناسِ يومَ القيامةِ ولا فخرَ ، وأنا أولُ من يدخلُ الجنَّةَ يومَ القيامةِ
‟እኔ በትንሳኤ ቀን የሰው ልጆች ሁሉ አለቃ ነኝ በዚህም ኩራት የለም (አልኮራም) እኔ በትንሳኤ እለት ጀነት የምገባው የመጀመሪያው ሰው ነኝ።”
(📗Silsilat As-sahiha by Albani 4/100)
عَنْ أَنَسِ بْنِ مَالِكٍ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ” آتِي بَابَ الْجَنَّةِ يَوْمَ الْقِيَامَةِ فَأَسْتَفْتِحُ فَيَقُولُ الْخَازِنُ مَنْ أَنْتَ فَأَقُولُ مُحَمَّدٌ . فَيَقُولُ بِكَ أُمِرْتُ لاَ أَفْتَحُ لأَحَدٍ قَبْلَكَ
አነስ ኢብኑ ማሊክ (ረ.ዐ) እንደተረከው የአላህ መልዕክተኛ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል:- ‟በየውመል ቂያማ ወደ ጀነት በር እሄዳለሁ፣ ጠባቂውም አንተ ማነህ ? ይለኛል ‟እኔ ሙሐመድ ነኝ” እለዋለሁ። እርሱም ‟ላንተ እንድከፍት ታዝዣለሁ፣ ካንተ በፊት ይህን በር ለማንም አልከፍትም” ይለኛል።
(📗Sahih Muslim, 197: Book 1, Hadith 392)
2- ነቢዩ ሙሐመድ ከባልደረቦቻቸው መካከል ገና በዚህ ዓለም ሳሉ የጀነት መሆናቸውን የመሰከሩላቸው ሰዎች ነበሩ (ይህ ደግሞ የምዕመናን የጀነት እጣፋንታ አያውቅም ነበር የሚለውን ትችት የሚያፈርስ ነው)
- عشَرةٌ في الجنَّةِ : أبو بكرٍ في الجنَّةِ وعُمَرُ في الجنَّةِ وعُثمانُ في الجنَّةِ وعلِيٌّ في الجنَّةِ والزُّبيرُ في الجنَّةِ وطَلحةُ في الجنَّةِ وابنُ عوفٍ في الجنَّةِ وسعدٌ في الجنَّةِ وسعيدُ بنُ زيدٍ في الجنَّةِ وأبو عُبَيدةَ بنُ الجرَّاحِ في الجنَّةِ
‟እነዚህ አስሩ የጀነት ናቸው። አቡበከር የጀነት ነው፣ ዑመር የጀነት ነው፣ ዑስማን የጀነት ነው፣ አሊይ የጀነት ነው፣ ዙበይር የጀነት ነው፣ ጦልሃ የጀነት ነው፣ ኢብኑ ዐውፍም የጀነት ነው፣ ሰዒድም የጀነት ነው፣ ኢብኑ ዘይድም የጀነት ነው፣ አቡ ዑበይዳም የጀነት ነው።
(📗Sahih ibn Hibban Hadith 7002)
3- የአላህ መልዕክተኛ እኛ ተከታዮቹ (በአላህ እና በመላዕክተኛው ያመንን ህዝቦች) ጀነት እንምንገባ በግልጽ ተናግረዋል (ይህ ደግሞ የምዕመናን እጣፋንታ ምን እንደሆነ አያውቅም የሚለውን ተራ ንግግር የሚንድ ነው)
عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم قَالَ كُلُّ أُمَّتِي يَدْخُلُونَ الْجَنَّةَ، إِلاَّ مَنْ أَبَى قَالُوا يَا رَسُولَ اللَّهِ وَمَنْ يَأْبَى قَالَ مَنْ أَطَاعَنِي دَخَلَ الْجَنَّةَ، وَمَنْ عَصَانِي فَقَدْ أَبَى
አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ) እንደተረከው የአላህ መልዕክተኛ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል ‟የኔ ተከታዮች ሁሉም ጀነት ይገባሉ፣ ከአስተባበዮች በቀር።” ሰዎችም ‟እነዚያ አስተባበዮች እነማን ናቸው?” አሉ። እሳቸውም ‟እኔን የታዘዘኝ ጀነት ገባ፣ የካደኝ ደግሞ ገሀነም ገባ” ብለው መለሱ።
(📗Sahih al-Bukhari, 7280: Book 96, Hadith 12)
ከእነዚህ ሐዲሶች በግልጽ እንደምንረዳው የአላህ መልዕክተኛ ጀነት መግባታቸውን እንደሚያውቁ እና በእምነት ላይ መልካም ስራ የነበራቸው ትውልዶች የጀነት መሆናቸውን አስቀድመው ማወቃቸውን ነው። አንድ ሰው በአላህ አምላክነት እና በነቢዩ መልዕክተኝነት ካመነ መልካምንም ስራ ከሰራ በአላህ ፍቃድ ያለ ጥርጥር ጀነት እንደሚገባ ጌታ አምላካችን በብዙ የቁርኣን ክፍሎች በተደጋጋሚ ቃል ገብቷል (85:11፣ 45:30፣ 84:25፣ 32:18…) ታድያ የምዕመናን ጀነት መግባት እርግጥ ከሆነ የአላህ መልዕክተኛም ጀነት መግባታቸውን አስቀድመው ከገለጹ የሚከተለው አንቀጽ ምን ማለት ፈልጎ ነው ? የሚለውን እንመልከት።
«…በእኔም በእናንተም ምን እንደሚሰራ አላውቅም፡ ወደእኔ የሚወረደውን እንጅ ሌላን አልከተልም…» (ሱረቱል አሕቃፍ 46፥9)
ይህ የቁርኣን አንቀጽ በፍጹም ስለ ቀጣዩ ዓለም ተስፋ (ጀነት ወይም ጀሀነም) እየተናገረ አይደለም። የአላህ መልዕክተኛ “በል” የተባሉት በቀጣዩ ዓለም የሚፈጠረውን ነገር ሳይሆን በዚህ ዓለም ላይ ስለሚከሰቱ ክስተቶች ነው። ማለትም እሳቸው ❝በእኔም በእናንተም ምን እንደሚሰራ አላውቅም❞ ያሉት በመጪው ዓለም የት እንደምንገባ አላውቅም እያሉ ሳይሆን በምኖርበት ዘመን የሚደርስብንን መከራ ስንኖር የሚያጋጥመንን ውጣ ውረድ አላውቅም እያሉ ነው። የአላህ መልዕክተኛ የሰው ልጅ በመሆናቸው እሳቸው ላይም ሆነ ሌሎቹ ላይ ወደፊት የሚመጣውን ነገር አያውቁም፣ አላውቅም ያሉትም በዚሁ ቀመር ነው። ጥንታዊያን ሙስሊም ሊቃውንት በዚህ መንገድ ያብራራሉ:-
من أول مبعثه إلى مماته يخبر أن من مات على الكفر مخلد في النار ، ومن مات على الإيمان واتبعه وأطاعه فهو في الجنة ، فقد رأى – صلى الله عليه وسلم – ما يفعل به وبهم في الآخرة . وليس يجوز أن يقول لهم ما أدري ما يفعل بي ولا بكم في الآخرة
‟ነቢዩ እድሜ ልኩን ከተመረጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከሞተበት ቀን ድረስ በክህደት ላይ ሆኖ የሞተ ሰው በቀጣዩ ዓለም በገሃነመ እሳት ውስጥ እንደሚዘወትር እንዲሁም አማኝ ሆኖ እርሱን የተከተለ ሰው በጀነት ለዘለዓለም እንደሚኖር ተናግሯል። ነቢዩ በመጪው ዓለም ምን እንደሚሰራ በእርግጥ አይቷል። ይህ አንቀጽ በፍጹም በቀጣዩ ዓለም (በአኼራ) ምን እንደሚፈጠር አላውቅም ማለትን አያሲዝም።
(📚ተፍሲር አል-ቁርጡቢይ ክፍል (ጁዝዕ) 16፣ ገፅ 186)
ታላቁ የቁርኣን ተንታኝ ኢብኑ ከሲር የታቢዕዩን ሀሰን አልበስሪን (641 AD) ዘገባ በመጥቀስ አንቀጹን በሚከተለው መንገድ ይተነትናሉ:-
وقال أبو بكر الهذلي عن الحسن البصري في قوله تعالى “وما أدري ما يفعل بي ولا بكم” قال أما في الآخرة فمعاذ الله وقد علم أنه في الجنة ولكن قال لا أدري ما يفعل بي ولا بكم في الدنيا أخرج كما أخرجت الأنبياء عليهم الصلاة والسلام من قبلي؟ أم أقتل كما قتلت الأنبياء من قبلي؟ ولا أدري أيخسف بكم أو ترمون بالحجارة؟ وهذا القول هو الذي عول عليه ابن جرير وأنه لا يجوز غيره ولا شك أن هذا هو اللائق به صلى الله عليه وسلم فإنه بالنسبة إلى الآخرة جازم أنه يصير إلى الجنة هو ومن اتبعه. وأما في الدنيا فلم يدر ما كان يؤول إليه أمره وأمر مشركي قريش إلى ماذا؟ أيؤمنون أم يكفرون فيعذبون فيستأصلون بكفرهم
አቡበከር አል-ሐዝሊይ ከሀሰን አልበስሪ ተቀብሎ እንደተረከው ‟በእኔም በእናንተም ምን እንደሚሠራም አላውቅም” የሚለው አንቀጽ ላይ (የሚከተለውን አስቀምጧል) አምላካችን አላህ በቀጣዩ ዓለም (አኼራ) ነቢዩ ሙሐመድ የጀነት ሰው መሆናቸውን አሳውቋል። እርሱም (ነቢዩ) ﷺ እንዳለው ‟በዚህች ዓለም (በዱንያ) በእኔም ሆነ በተከታዮቼ ላይ የሚደርሰውን መከራ እንደ ቀደምት ነቢያት ከሀገር ልባረር ወይም ይግደሉኝ እንዲሁም እናንተ ላይ የሚደርሰውን ነገር አላውቅም” በማለት ተናግሯል። የአላህ መልዕክተኛ በቀጣዩ ዓለም እርሱም ሆነ ተከታዮቹ በጀነት እንደሚኖሩ አስቀድሞ ከተገለፀ ይህ አንቀጽ ስለዚህች ዓለም ማውራቱ ምንም ጥርጥር የለውም። ስለ ዱንያ ግን ወደፊት ምን እንደሚሆን አያውቅም፣ ቁረይሾች ይመኑ ይካዱ፣ በክህደታቸው ላይ ሆነው ይሙቱ መጪውን ነገር አያውቅም።
(📚ተፍሲር ኢብኑ ከሲር ቅጽ 4፣ ገፅ 168)
وَمَا أَدْرِي مَا يُفْعَل بِي وَلَا بِكُمْ فِي الدُّنْيَا أَأَخْرُجُ مِنْ بَلَدِي أَمْ أُقْتَل كَمَا فُعِلَ بِالْأَنْبِيَاءِ قَبْلِي أَوْ تَرْمُونِي بِالْحِجَارَةِ أَمْ يُخْسَف بِكُمْ كَالْمُكَذِّبِينَ قَبْلكُمْ
ማለትም በዚህች ዓለም (በዱንያ) በእኔም ሆነ በሕዝቦቼ ላይ የሚከሰተውን አላውቅም። ከሀገሬ ያስወጡኝ ወይም ልክ እንዳለፉት ነቢያት ወግረው ይግደሉኝ እናንተንም እንዳለፉት አስተባባዮች ምድር ትውጣችሁ ምንም የማውቀው ነገር የለኝም።
(📚ተፍሲር አል-ጀላለይን ቅጽ 1፣ ገፅ 667)
ስናጠቃልል:- በቁርኣን ምዕራፍ 46:9 ላይ የአላህ መልዕክተኛ በእኔም ሆነ በእናንተ ላይ ምን እንደሚሰራ (እንደሚፈጠር) አላውቅም ያሉት በመጪው ዓለም (በአኼራ) መኖሪያችንን አላውቅም እያሉ ሳይሆን የሰው ልጅ እንደመሆናቸው በምድራዊ ሕይዎታቸው እሳቸውንም ሆነ ሕዝባቸውን ምን እንደሚያጋጥማቸው (እንደሚመጣባቸው) አላውቅም እያሉ ነው፣ እንጂ በፍጹም ስለ መጪው ዓለም እጣፋንታ እየተናገሩ አይደለም። ያ እንዳልሆነ የምታቁት አንደኛ:- በተደጋጋሚ በመጪው ዓለም ጀነት ከሚገቡት ቀዳማዊ ሰው መሆናቸውን በመግለጻቸው እና እሳቸውን የተከተሉት ሕዝቦች እጣፋንታቸው ጀነት መሆኑን በመናገራቸው ነው። ሁለተኛ:- በዚሁ በተነሳው የቁርኣን አንቀጽ ላይ በጥንታዊያን ትውፊቶች በተላለፉልን ዘገባዎች ውሰጥ እሳቸው ስለ ምድራዊ ሕይወት መናገራቸው ተገልጿል። ስለዚህ ሙግቱ ውድቅ ነው። አላህ ሒዳያ ይስጣችሁ።
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


