ወንድም ሳላህ
ጌታ አምላካችን ታላቁን ቁርኣን እራሱ አውርዶ ለጥብቅናውም ሀላፍትና እንደወሰደ ቃል መግባቱን ነግሮናል (ሱራ 15:9)። በቃሉ መሰረትም ለ1400+ ዓመታት ከፊቱም ሆነ ከኃለው ውሸት ሳይገባበት ከላዩ ላይም አንድም እውነት ሳይቀነስ እንዲሁም ከነቢዩ ሙሐመድ የሕይወት ዘመን ጀምሮ እስከዛሬዋ እለት ድረስ ቃል በቃል ፊደል በፊደል ከነ ተጅዊዳዊ ንባቡ ጋር ተጠብቆ እንደሚገኝ እኛ ሙስሊሞች ክፉኛ እናምናለን። እምነታችንን የሚያጠናክሩልን እጅግ ብዙ ማሳያዎች ቢኖሩም ከእነርሱ ውስጥ በነቢዩ በኩል በሒፍዝ ደረጃ (በሽምደዳ መልኩ) ቃል በቃል የመጣው የቁርኣን ንባብ አንዱ ማሳያ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በዚያው በኸሊፋዎች ዘመን የተጻፉ የኡስማን ቅጂዎች ከመጀመሪያው የሒጅራ ክፍለዘመን ተጠብቀው መገኘታቸው ከበቂ በላይ የሚሆኑ ማስረጃዎች ናቸው።
ይህን እውነታ ለመደበቅ ሙስሊም ያልሆኑ አካላት በተለይ ክርስቲያን ሰባኪዎች ቁርኣንን ጥያቄ ውስጥ አስገብተው ከተበረዘው መጽሐፋቸው ጋር እኩል ለማድረግ ብዙ እርቀት ተጉዘዋል። እጅጉንም ለፍተዋል፣ ትችትን መተዳደሪያቸው አድርገው ሌት ከቀን እንቅልፋ አጥተውለታል። ያልፈነቀሉት ድንጋይም ሆነ ተራራ የለም ቢባል እብለት አይሆንም። ሐሰት ቢደራጅ፣ ቢተባበር እና ሺ ዓመታት ቢቀናጅ በአንድ ደቂቃ ይፈርሳልና የሚሺነሪዎቹ ድካም እንደምናየው ከግብ ሳይደርስ ቀርቷል። እስኪ ዛሬም እንደው ከተሳካልን ብለው ለጠቀሱት ሙግታቸው ምላሽ እንስጥ።
ሚሺነሪዎቹ ኪታብ አል-መሳሒፍ ላይ የተዘገበው ታሪክ በመጥቀስ ‟ሐጃጅ የተባለው ጥንታዊው ገዥ ከኡስማን ሙስሐፍ 11 የቁርኣን ቃላት ላይ ለውጥ አድርጓል ስለዚህ ቁርኣን ቃል በቃል ተጠብቋል የምትሉት ነገር ከእውነት የራቀ ንግግር ነው” ብለው ይናገራሉ። በዚህ ጹሑፍ ሰባኪዎቹ ያነሱት ታሪክ ምን ያክል ይደግፋቸዋል ? ምን ያክልስ ተዓማኒ ነው የሚሉትን ነጥቦች እንመለከታለን። እስኪ መጀመሪያ አል-ሐጃጅ ቀየራቸው የተባሉትን ቃላት ከጠቀሱት መጽሐፍ እንመልከት:-
❝ዐባድ ኢብኑ ሱሃይብ ከዐውፍ ኢብኑ ጀሚላ ተቀብሎ እንደተረከው ‟አል-ሐጃጅ ኢብኑ ዩሱፍ ከኡስማን ሙስሐፍ ላይ አስራ አንድ ቃላትን ቀይሯል” እነርሱም:- በሱረቱል በቀራ ላይ ‟ለም የተሰና” لَمْ يَتَسَنَّ የሚለውን ወደ “ለም የተሰናህ” لَمْ يَتَسَنَّهْ ቀይሮታል። በማዒዳህ ላይም ‟ሸሪዐተን ወሚንሃጃ” شَرِيعَةً وَمِنْهَاجًا የሚለውን ቃል ወደ ‟ሺርዐተን ወሚንሃጃ” شِرْعَةً وَمِنْهَاجًا ቀይሯል። በሱረቱል ዩኑስ ላይም “የንሹሩኩም” يَنْشُرُكُمْ የሚለውን ወደ “ዩሰዪሩኩም” يُسَيِّرُكُمْ ቀይሯል። በዩሱፍ ሱራ ላይም ‟አነ ኣቲኩም” أَنَا آتِيكُمْ የሚለውን ቃል ወደ “አነ ኡነቢዑኩም” أَنَا أُنَبِّئُكُمْ ቀይሮታል….❞ [የቀሩትን ምሳሌዎች ከታች በፎቶ ይመልከቱ]
(📗ኢብኑ አቢ-ዳውድ: ኪታብ አል-መሳሒፍ ገፅ 59)

ጹሑፍ ላለማንዛዘት አስራ አንዱንም ተቀይሯል የተባሉትን ቃላት ከመጽሐፉ ገፅ በፎቶ አስቀምጥላችኃለው። እውን “አል-ሐጃጅ 11ዱ ቃላት ላይ ለውጥ አድርጓልን ወይስ የሐሰት ታሪክ ተላልፎ ነው ?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ ግድ ነውና ቀጥታ ወደ ምላሹ እንምጣ:-
1- ከሁሉም በፊት ማወቅ ያለብን ነገር በኪታብ አል-መሳሒፍ ላይ የተቀመጠው ሪዋያ ተቀባይነት ያሌላው “ደዒፍ” ዘገባ መሆኑን ነው። በስነ-ሐዲሳት (Hadith terminology) ጥናት መሰረት በአንድ ኢስናድ “Chain of narration” ውስጥ ከሚገኙት አስተላለፊዎች መካከል በሊቃውንት ዘንድ “መትሩክ” (Abandoned) የሆነ ሰው ካለ ዘገባው በፍጹም ተቀባይነት አይኖረውም። ታድያስ ይህ ዘገባ ውድቅ እንዲሆን ያደረገው ሰው ማነው ከተባለ በሰነዱ ላይ የምንመለከተው “ዐባድ ኢብኑ ሱሃይብ” የተባለው ሰው ነው። እስኪ የሐዲስ ሊቃውንት ስለዚህ ሰው ምን አሉ ? የሚለውን እንመልከት:-
▹ ኢማም አል-ቡኻሪ በዱዐፋእ አል-ሰጚር ውስጥ እንዲህ በማለት ይነገራል። ‟ዐባድ ኢብኑ ሱሃይብ የተተወ ተቀባይነት ያሌላው (Abandoned) ሰው ነው ተውት።
(Al-Bukhari, Kitab Duafa al-Saghir [1396 AH] Page 76)
▹ አል-ኒሳዒም በተመሳሳይ በዱዐፋእ ወል-መትሩኪን መጽሐፉ ላይ እንዲህ በማለት ይናገራል ‟ዐባድ ኢብኑ ሱሃይብ የእርሱ ሐዲሶች የተወገዙ ናቸው “His hadith is rejected” (መትሩክ አል-ሐዲስ)
(Al Nasa’i ,Kitab al-Duafa wa-l-Matrukin, page 75)
▹ ኢብኑ አቢ ሃቲም በመጽሐፉ ኪታብ አል-ጀሕር ወት-ተዕዲል ላይ የሚከተለውን አስቀምጧል ❝…He said:- ‘His hadith is weak (daif). His hadith is disavowed (munkar). His hadith is forsaken…ስለ ዐባድ ኢብኑ ሱሃይብ አባቴን ጠይቄ እንዲህ አለኝ ‟የእርሱ ዘገባዎች ደዒፍ ናቸው፣ ሐዲሶቹ ተቀባይነት ያሌላቸው ሙንከር (የተተው) ናቸው❞
(Kitab al-Jarh wa-l-Tadil, 1941-53, Volume 3, p. 81-82)
[፨] እንደምትመለከቱት የሐዲስ ሊቃውንት የዘገባው ባለቤት የሆነው አካል ተቀባይነት ያሌላው ሰው መሆኑንና የእርሱ ሐዲሶችም የተወገዙና የተተው መሆናቸውን ነግረውናል። በአጭሩ የዚህን ዘጋቢ ሐዲስ ይዞ ለሙግት መነሳት ፈጽሞ የማይቻል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የሐዲሱን ደረጃ በተመለከተ ሙሂቡ ዲን በኪታቡል መሳሒፍ ላይ በሰጡት ደረጃ ሰነዱ እጅግ ደካማ (Very weak) መሆኑን ገልጸዋል።
(Kitab Al-masahif, Ibn abi dawud, [Dar al-basha’ir] by Muhibu Ad-din Vol.1 p.280)
2- አል-ሐጃጅ የኡስማንን ሙስሐፍ የሚከተልና እጅጉንም የሚስማማበት ሰው በመሆኑ ቃላትን የሚቀይርበት ምንም አይነት ምክንያት የለም። ኢማሙ ነወዊይ እንዲህ በማለት ይናገራሉ:-
أَنَّ الْحَجَّاجَ إِنَّمَـا كَانَ يَتَّبِعُ مُصْحَفَ عُثْمَـانَ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُ وَلَا يُخَالِفُهُ
‟አል-ሐጃጅ የኡስማንን ሙስሐፍ ይከተል ነበር፣ ከእርሱም ጋር ምንም አይነት ተቃርኖ (አለመስማማት) አልነበረውም።
(📗ሶሂህ ኢማሙ ሙስሊም ኢብኑ ሐጃጅ ቢሸርህ አን-ነወዊይ ቅጽ 9፣ ገፅ 62)
3- አል-ሐጃጅ አንድንም ቃል የሚቀይርበት ምክንያትም ሆነ መንገድ የለም። ይህ ሰው ይኖርበት የነበረው ዘመንና ቦታ ቁርኣንን አይደለም መቀየር ይቅርና ትርጉሙን ማጣመም እንኳ የሚያስገድልበት የኸሊፋው ዘመን በመሆኑ ቀይሮ ቢሆን ኖሮ በሕይወት እንኳን ባልተረፈ ነበር። እንደው በግድ ቀይሯል ቢባል እንኳ ይህ ሰው አንድንም ባዕድ ሀሳብ ወይም ቃል አልጨመረም። ሁሉም ቁርኣናዊ የሆኑ በሌሎች አስርቱ የአቀራር ዘዴዎች ውስጥ የሚገኙ ቃላት ናቸው¹:: ዳሩ ግን ቀይሯል የሚለው ዘገባ ከመሰረቱ ተቀባይነት ያሌለው ታሪክ ነው። ተቀባይነት ቢኖረው እንኳ የሚያመጣው ለውጥ የለም።
1- Dr. `Umar Ibn Ibrahim Radwan, Aara’ al-Mustashriqin Hawl al-Qur’an al-Karim wa Tafsir: Dirasah Wa Naqd, Volume I, 1992, Dar al-Tibah: Riyadh, p. 430.
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


