ወንድም ሳላህ
አምላካችን አላህ ታላቁን መልዕክተኛ ነቢዩ ኢየሱስን “መሲሕ” በሚለው የማዕረግ ስሙ ወደ 9 ጊዜ በተደጋጋሚ ይጠቅሰዋል። በሱረቱል አሊ-ዒምራን አንቀጽ 45 ላይ መላእክት የብስራትን ዜና ለማሪያም ይዘው ሲመጡ የሚወለደው ልጅ ስሙ “መሲሕ” ተብሎ እንደሚጠራ አስቀድመው ተናግረዋል። እስኪ ይህ የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ማዕረግ በኢስላም የስሙ ትርጓሜ ምንድነው ? አላህ ለዒሣ ለምን ይህንን ለቀብ “title” ሰጠው? የሚለውን ነጥብ እንመልከት:-
‟አል-መሲሕ” الْمَسِيح የሚለው ስም “መሰሀ”مَسح ማለትም “ዳበሰ” “ቀባ” ከሚለው ስርዎ-ቃል የመጣ ሲሆን “የተቀባ፣ የተዳበሰ፣ የተመረጠ፣ የተባረከ” ማለት ነው። በአንዳንድ ሊቃውንት ዘንድ ‟መሲሕ” مَسِيح የሚለው ስም ‟መሺያኽ” מָשִׁיחַ ከሚለው የእብራይስጥ ስም ሙዐራብ (Arabized) እንደተደረገ ይታመናል። ታድያስ ኢየሱስ በዚህ ስያሜ ለምን ተሰየመ ? ለሚለው ጥያቄ ቀደምት አበዎች የተለያዩ አንድምታዎችን ያስቀምጣሉ ከእነርሱ ውስጥ:-
أن الله مَسَحه فطهره من الذنوب
1- ኢየሱስ (መሲሕ የተባለበት ምክንያት) አላህ እርሱን ዳብሶት ከኃጢአት ስላነጸው ነው የሚለው አንዱ ነው።
لأنه ممسوح البركة
2- (መሲሕ የተባለው) እርሱ (ኢየሱስ) በበረከት ስለተዳበሰ (ስለተቀባ) ነው ብለው የሚፈቱትም ጥቂቶች አይደሉም።
لأنه كان إذا مسح بيده على أهل العاهة ، أفاقوا
3- መሲሕ በሚለው ማዕረግ የተጠራበት ምክንያት እርሱ (ኢየሱስ) ሕመምተኞችን በዳበሰ ጊዜ ስለሚፈወሱ ነው የሚለው አመለካከትም በሰፊው ይታመንበታል።
ጁሙሑር ኡለማዕ ኢየሱስ መሲሕ የተባለው በአላህ ፍቃድ በተለያዩ በሽታዎች የተያዙትን ሰዎች በሚዳብስበት ጊዜ ስለሚፈወሱ እንደሆነ ያምናሉ። የዘመናችን ታላቁ ዓሊም ኢማም ኢብኑ ባዝ በዚሁ ርዕስ ላይ እንዲህ በማለት ይናገራሉ:- ❝የአላህ ሰለዋት (በረከት) እና ሰላም በእርሱ ላይ ይሁንና ኢየሱስ መሲሕ ተብሎ የተጠራው ልክ በቁርኣን 3:49 ላይ እንደተነገረን ዓይነ-ስውራንና ለምጻሞችን በዳበሰ ጊዜ አላህ ነጻ ስለሚያደርጋቸው ነው። … ደጃል (Anti-Christ) ደግሞ “መሲሕ” የተባለበት ምክንያት ምድርን በመከራ ስለሚዳብስ (ስለሚዞር) ነው❞
(📘ኢማም ኢብኑ ባዝ: ኑር አል-ደራብ: ኢየሱስ ለምን መሲሕ ተባለ ከሚለው ምዕራፍ የተወሰደ)
አቡል በረካት አል-ነሰፊይ እና ሌሎችም ጥንታዊያን ሙስሊም ሙፈሲሮች እንዲህ በማለት ይናገራሉ:-
والمسيح لقب من الألقاب المشرفة كالصديق والفاروق وأصله مشيحا بالعبرانية ومعناه المبارك
‟አል-መሲሕ ከአክብሮት ማዕረጎች መካከል አንዱ ሲሆን ልክ ሷዲቅ እና ፋሩቅ እንደሚባለው ነው። መሰረቱም መሺይኸ የሚል የእብራይስጥ ስም ሲሆን ትርጓሜውም “የተባረከ” ማለት ነው።
(📗Tafsir Al-Nasafi Vol.1 Page 154)
ስለዚህ ኢየሱስ መሲሕ ተብሎ የተጠራው በአምላክ ስለተመረጠ፣ በበረከት ስለተቀባ፣ በአምላክ ኃይል ሕመምተኞችን ከበሽታቸው ስለፈወሰ ነው። ሌላ ምንም አይነት አንድምታ የለውም። አንዳንድ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ብቻውን መሲሕ መባሉ መለኮትነቱን ያሳያል ይላሉ ! ምጽ። በመጀመሪያ ከቃሉ ጀርባ ያንን የሚያሲዝ ትርጉም አለመኖሩን የምታውቁት የኢየሱስ ተቃዋሚ የሆነው ደጃል እንኳ “መሲሕ” ተብሎ በመጠራቱ ነው። ሁለተኛ በገዛ መጽሐፍቶቻችሁ በአምላክ የተመረጡ አያሌ ሰዎች “መሲሕ” ተብለው መጠራታቸው ነው። እስኪ ለጊዜው አንዱን ብቻ እንመልከት:-
“እግዚአብሔር ለቀባሁት፥ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ የነገሥታትንም ወገብ እፈታ ዘንድ፥ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ፥ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል፦”
— ኢሳይያስ 45፥1
‟ለቀባሁት” የሚለው ቃል በእብራይስጡ ‟ለሚሽኾ” לִמְשִׁיחוֹ֮ ሲሆን “ለመሲሑ” To his anointed ማለት ነው። ቄርሎስ ዘአሌክሳንደሪያ በዚሁ ጥቅስ ላይ በሰጣው ማብራሪያ ማንም ቅዱስ እንኳ ባይሆን በአምላክ የተመረጠ ሰው “መሲሕ” እንደሚባል ይገልጻል።
(Ancient Christian Commentary on Scriptures XI p. 71)
ይህ ማዕረግ በብሉይ ኪዳን እነ ሳኦል እንኳ የተጠሩበት የክብር አጠራር መሆኑ ባይብልን ከሚያነብ ሰው የሚሰወር ታሪክ አይደለም። አምላክ ኃይልንና ስልጣንን የሚሰጥ ነው፣ ፍጡር ደግሞ ያንን ስልጣን የሚቀበል ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን በኃይል እንደቀባው (መሲሕ እንዳደረገው) ባይብል ይናገራል:- ❝እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ።”
— ሐዋርያት 10፥38 (አዲሱ መ.ት)
ፈጣሪ ቀቢ፣ ሿሚ፣ መራጭ ከሆነ ተቀቢው፣ ተሿሚው፣ ተመራጩ ደግሞ ፍጡር ይሆናል ማለት ነው። አላህ ፍጡርን ከማምለክ ይጠብቀን።
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


