ወንድም ሳላህ
ሚስዮናዊያን ቁርኣን ላይ ከሚከፍቷቸው ክሶች መካከል ‟ቁርኣን ከፊቱ ያለውን ታሪክ ከሌላ ጹሑፍ ገልብጧል (ኮርጇል)” የሚል ነው፣ ይህ ክስ ጥንትም በቁረይሾች ተነስቶ እንደነበር ይታወቃል፣ ዛሬም በምዕራቡ ዓለም ሰባኪዎች እና በአንዳንድ የሃገራችን ወገኖች በተደጋጋሚ ይነሳል። ተኮርጇል ተብሎ የሚቀርበውን ታሪክና የተኮረጀበት ቀዳሚው ምንጭ ይህ ነው ብለው ሲያቀርቡ ሁሌም ግርም ይለኛል። ለማንኛውም ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ስንመጣ ገብርኤል ሳይድ ሪይኖልድስ የተባለው ጸሐፊ “The Qur’an in Its Historical Context” በተሰኘው መጽሐፉ ገጽ 175-80 ላይ ቁርኣን የዙልቀርነይንን ታሪክ ከሲሪያኩ ጹሑፍ ‟ኒሻነህ ዲሌህ አሌክሳንድሮስ” ወይም “የአሌክሳንደር ግሩም ስራዎች” በመባል ከሚታወቀው ጹሑፍ ነው የተቀዳው በማለት ይጽፋል።
ይህ የሲሪያክ ጹሑፍ ልክ እንደ ቁርኣኑ (18:83-94) የዙልቀርነይንን ኀይል መሰጠቱን (ማግኘቱን)፣ ወደ ምዕራቡ ውቂያኖስ አከባቢ ጉዞ ማድረጉን፣ መጥፎ ሰሪዎችን መቅጣቱን፣ መጠለያ ያሌላቸው ህዝቦች ላይ የፀሐይን መውጣት፣ በሁለት ተራሮች መካከል ወደሚገኘው ሸለቆ መሄዱንና ስለ የዕጁጅ እና መዕጁጅን ወሬ መስማቱን፣ እንዲሁም በእነርሱ ላይ የብረትን ግንብ መገንባቱን በውስጡ ይዘክራል።
(The History of Alexander the Great, Being the Syriac Version, p.146-153)
ምንም ያክል ቁርኣን ውስጥ ያሌሉትን ታሪኮች ጨምሮና ቀንሶ ቢያቀርብም ከቁርኣኑ ጋር የሚያመሳስለው ነገር አለው፣ ይህ “The Glorious Deeds of Alexander” የተባለው ጹሑፍ ነቢያችን ሙሐመድ ነቢይ ከሆኑ ቡኋለ ቆይቶ የተሰማ ሲሆን ሱረቱል ከሐፍ ወርዶ ከተሰራጨ ረጅም ዓመታት ቡኋለ የተጻፈ ታሪክ ነው። ሱረቱል ከሕፍ የመካ ምዕራፍ ‟መኪይ”مَكِّيّ ሲሆን የነቢያችን ሰሃቦች ወደ ኢትዮጵያ ሒጅራ ከማድረጋቸው በፊት የወረደ ነው፣ ስለዚህ የቁርኣኑ አንቀጽ አስቀድሞ በነቢያችን ላይ ከመጀመሪያው ስደት (615 CE) በፊት መውረዱን በቀላሉ መረዳት እንችላለን። ምሁራን ሱረቱል ከሕፍ መቼ እንደወረደ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ:-
فإن سورة الكهف نزلت قبل الهجرة إلى المدينة بمكة المكرمة كما قال ابن عباس، ويرى بعض الباحثين أنها نزلت قبل الهجرة الأولى إلى الحبشة، وعليه يكون نزولها في السنة الخامسة للبعثة
‟ሱረቱል ከሐፍ የወረደችው በመካ ስትሆን ወደ መዲና ሒጅራ ከመገደረጉ አስቀድሞ ነው፣ ኢብኑ አባስና ሌሎችም ምንጮች እንደሚነግሩን ከመጀመሪያው የኢትዮጵያ ስደት (ሒጅራ) በፊት ሲሆን ይህም ነቢያችን ከተነሱ አምስት ዓመታት ቡኋለ ማለት ነው።
(🌐Islamweb: Historical background of surah Al-khaf Nō of fatwa 40008)
በእስልምና የመጀመሪያው ሒጅራ የሚባለው ወደ ኢትዮጵያ የተደረገው ስደት ሲሆን 615 አከባቢ ነው፣ ሱረቱል ከሐፍ ደግሞ ከዚያ አስቀድሞ የወረደ አንቀጽ መሆኑን እንረዳለን። ስለዚህ በእስልምና የዙልቀርነይን ታሪክ የተነገረን ከ615 CE በፊት መሆኑ የማያከራክር ጉዳይ ነው። ይህ ቁርኣን ከእርሱ ኮርጇል የተባለው የሲሪያኩ ጹሑፍ ደግሞ በ629-30 CE ላይ እንደተጻፈ እራሳቸው ይህንን ክስ የሚያቀርቡት ሰዎች እንኳ አይክዱም፣ እንደውም የሀገራችን ሰባኪዎች በቅርቡ ስለ ዙልቀርነይን በጻፉት አርቲክል ላይ የዚያን ጹሑፍ እድሜ በተመለከተ የሬኒንክን መጽሐፍ ጠቅሰው እንዲህ ይላሉ ❝እንደ ሬኒንክ ያሉ በዘርፉ ሰፊ ጥናት ያካሄዱ ምሁራን እንደሚገልጹት ይህ አፈታሪክ የተጻፈው ሮማውያን ከፋርሶች ጋር ያደረጉት ጦርነት ማብቂያ 628-630 AD አካባቢ ነው❞
በዚህ ዘርፍ ላይ ጥናት ያካሄዱት ምሁራን ይህ ‟የአሌክሳንደር ግሩም ስራዎች” የተባለው የሲሪያክ ጹሑፍ የተጻፈው ሙስሊሞች ሞሰፖታሚያንና ፍልስጤምን ከመቆጣጠራቸው ጥቂት ዓመት አስቀድሞ መሆኑን ይገልፃሉ ‟The poem, however, was actually written in the seventh century, shortly before the Muslim conquest of Mesopotamia and Palestine [1]። ይህ ደግሞ በ638 AD አከባቢ እንደሆነ ታሪክ ይናገራል። ያ ማለት ሱረቱል ከሐፍ ከወረደ 15 ዓመታት በላይ ቆይቶ የተዘጋጀ ጹሑፍ መሆኑን በቀላሉ መረዳት እንችላለን። ታድያስ በየትኛው መንገድ ነው ነቢያችን ገና ተጽፎ ከማይታወቅ ጹሑፍ የሚገለብጡት ? የቁርኣኑ አንቀጽ ወርዶ በዓለም ከተሰራጨ 15 ዓመታት በላይ ቆይቶ የተጻፈው ታሪክ እንዴት ለቁርኣን መሰረት ይሆናል ? ልጅ አባቱን ቀደመ አይነት ውዥንብር ሙግት ማንሳት የምታቆሙበት ቀን መች ይሆን ?
ሌላኛው መታየት ያለበት ትልቁ ነጥብ የአሌክሳንደር ግሩም ስራዎች ጹሑፋዊ ተዓማኒነት” Textual reliability of The Glorious Deeds of Alexander የሚለው ነጥብ ሲሆን ክርስቲያን ሚሺነሪዎች ያነሱት ገለባ ክስ በዚህ ክፍል የድንጋይ አመድ መሆኑን በቀላሉ ማየት ትችላላችሁ። ከላይ እንዳልነው ይህ ከቁርኣን ጋር ትንሽ መመሳሰል የሚታይበት ጹሑፍ የተጻፈው በ630 AD አከባቢ ይሁን እንጂ አንድም ጥንታዊ የእጅ-ጹሑፍ “Manuscript” የለውም። አይደለም የሰባተኛው ክፍለዘመን እደ-ክታብ ሊኖረው ይቅርና የ15ኛው Century ጹሑፍ የለውም፣ እንደሚታወቀው ታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ የተጻፈው በሲሪያክ ቋንቋ ነው፣ ጥንታዊ የሚባሉት የሲሪያኩ የእጅ-ጹሑፎች አምስት ሲሆኑ ከእነርሱ ውስጥ ቀደማዊ የሚባለው ራሱ በ18ኛው ክፍለዘመን የተሰበሰበው ነው። The Syriac version of the Alexander Romance is preserved in five manuscripts, the oldest was compiled in 1708-09 AD. [2]
እንደምታዩት የጹሑፉ ጥንታዊ እደ-ክታብ ከቁርኣን ቡኋለ ከአንድ ሺ ዓመታት በላይ ቆይቶ ነው የተጻፈው፡ ይህ ደግሞ ጹሑፋዊ ተዓማኒነቱን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፣ የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ በዚህ የሲሪያክ ጹሑፍ ላይ በየግዜው የሰው እጅ ይገባበታል፣ ጭማሬዎችና ስረዛዎች ያጋጥሙታል፣ ዊልስ በጅ የተባለው የጥንታውያን ጹሑፍ አጥኚ እንዲህ ይላል ‟The Christian Legend has been burdened with many additions..On the other hand many passages have been entirely omitted [3]
በዚሁ በሲሪያኩ ጽሑፍ ዙርያ ጥናት ያደረጉት ምሁራን ጭራሽ ጥንታዊያን የሚባሉት የግሪክ፣ የላቲን፣ የሲሪያክ እና የአርሜንያ የእጅ-ጽሑፎች ቅጂ ላይ አሌክሳንደር በጎግ እና ማጎግ ላይ ግንብ መገንባቱን ፈጽሞ አይናገሩም፣ ይልቁንም ይህ ታሪክ በጽሑፉ ላይ ከጊዜ ቡኋለ የተጨመረበት ብለው ነው የሚያምኑት። ‟The episode of Alexander’s building a wall against Gog and Magog, however, is not found in the oldest Greek, Latin, Armenian and Syriac versions of the Romance… the barrier episode has not its origin in this text” [4]
ይህ ቁርኣን ከእርሱ ወስዷል የተባለው የሲሪያኩ ጽሑፍ በትውፊት (Tradition) ደረጃ ነው በ7ኛ ክፍለዘመን ተጽፏል የተባለው እንደዛም ሆኖ ከቁርኣን አይቀድምም። ወደ እውነታው ስንመጣ ግን ይህ ጽሑፍ ከመካከለኛው ዘመን መጠናቀቅ ቡኋለ ነው ከብዙ ጭማሪ ጋር የተጻፈው። ጥንታዊው ብራናው እንኳ ዘመነ-መሳፍንትን የማይቀድም የቅርብ ጊዜ ጽሑፍ ነው። ከቁርኣኑ ጋር ስታነጻጽሩት ቁርኣን ከዚህ ጽሑፍ ያለ አንዳች ጭማሪ እና ቅነሳ በአሥር ክፍለዘመናት በላይ ይቀድመዋል፣ ይህም ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ ማለት ነው።
- ስናጠቃልል ቁርኣን ከአምላክ ዘንድ የወረደ ግልጠተ-መለኮት ነው፡ ከማንም እና ከምንም አልተኮረጀም፣ ስለ አሌክሳንደር የሚናገረው የሲሪያኩ ጹሑፍ ሱረቱል ከሐፍ ከወረደ ረጅም ጊዜ ቡኋለ የተጻፈ እንጂ ከቁርኣን ቀድሞ ለቁርኣን መሰረት ሊሆን የሚችል አይደለም። ምክንያቱም የተጻፈበት ጊዜ እስልምና በዓለም እየተስፋፋ ባለበት ወቅት ነውና፣ ቁርኣኑ ደግሞ በነጋዴዎችና በቃሪዖች ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰራጨበት ሰዓትም ስለነበር ምናልባት አንዱ የራሱን ሀሳብ ጨምሮ ገልብጦት ሊሆን ይችላል፣ ያለው የመጨረሻው መላምት ይህ ብቻ በመሆኑ የሲሪያኩ ጹሑፍ ከቁርኣን ካልገለበጠ ከየት አመጣው የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያገኝ አይደለም። የአሌክሳንደርን ግሩም ስራዎች የሚናገረው የሲሪያኩ መጽሐፍ የበኩር ጹሑፍ ያሌላው ብሩዝ (የተበረዘ) መዝገብ መሆኑ ደግሞ ነገሩን ይበልጥ ቀላል ያደርገዋል፡ የተነሳው ክስ ውሃ የማይቋጥር ደካማ ሙግት ነው።
▸[1] S.gero, “The Legend Of Alexander The Great In The Christian Orient” 1993, Volume 75, p. 7.
▸[2] Ciancaglini Claudia (2001) “The Syriac Version of the Alexander Romance” 121–140.
▸[3] Wills Budge, The History Of Alexander The Great Being The Syriac Version Of ThePseudo-Callisthenes, op cit., p. 77
▸[4] Donzel, Emeri J. van; Schmidt, Andrea Barbara (2010). Gog and Magog in Early Eastern Christian and Islamic Sources: Sallam’s Quest for Alexander’s Wall. Brill. p.17
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


