ወንድም ሳላህ
መካ በእስልምና ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው እና ቅዱስ ከሆኑ የአምልኮ ስፍራዎች ግንባር ቀደሟ ሀገር (ከተማ) ናት። ጌታ አምላካችን በክብር አልቆ የማለበት ሀገር (ሱራ 90:1) ከመሆኗም ባሻገር የነቢያቶች አባት የሆኑት አብረሃም ጸጥተኛ (የሰላም) ሀገር ትሆን ዘንድ በጸሎታቸው ያሰቧት ቅድስት ስፍራ ናት (ቁርኣን 2፥126)። በዚህች ጸጥተኛ ከተማ (መካ) ውስጥ ነቢዩ አብረሃም ከልጁ ኢስማኤል ጋር ለሰዎች የአምልኮ ቦታ ይሆን ዘንድ የቤተመቅደስን መሰረት ከፍ አድርገው እንዳቆሙ (እንደገነቡ) ቁርኣን እንዲህ በማለት ይናገራል:-
وَإِذْ يَرْفَعُ إِبْرَاهِيمُ الْقَوَاعِدَ مِنَ الْبَيْتِ وَإِسْمَاعِيلُ رَبَّنَا تَقَبَّلْ مِنَّا إِنَّكَ أَنتَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ
ኢብራሂምና ኢስማኢልም «ጌታችን ሆይ! ከእኛ ተቀበል፡፡ አንተ ሰሚውና ዐዋቂው አንተ ነህና» የሚሉ ሲኾኑ ከቤቱ መሠረቶቹን ከፍ ባደረጉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ (Qur’an 2:127)
አምላካችን አላህ ይህን ቤተመቅደስ በውስጡ ለሚዞሩትና ለሚቆሙበት፣ ለሚያጎነብሱትና ለሚሰግዱት ባሮቹ ንጹሕ እንዲያደርግ አብረሃምን እንዲህ በማለት ያዘዋል:-
وَإِذْ بَوَّأْنَا لِإِبْرَاهِيمَ مَكَانَ الْبَيْتِ أَن لَّا تُشْرِكْ بِي شَيْئًا وَطَهِّرْ بَيْتِيَ لِلطَّائِفِينَ وَالْقَائِمِينَ وَالرُّكَّعِ السُّجُودِ
ለኢብራሂምም የቤቱን (የካዕባን) ስፍራ መመለሻ ባደረግንለት ጊዜ «በእኔ ምንንም አታጋራ፣ ቤቴንም ለሚዞሩትና ለሚቆሙበት ለሚያጎነብሱትና በግንባራቸውም ለሚደፉት ንጹሕ አድርግላቸው» (ባልነው ጊዜ አስታውስ)፡፡ (Qur’an 22:26)
ይህ በአብርሃም የተገነባው ቤተ-አምልኮ ‟ከዕባ” كَعْبَةَ ተብሎ ይጠራል። ምንም ያክል ከአብርሃም በፊትም ስፍራው በቅድስናው ይታወቅ ነበር ተብሎ ቢታመንም በሰፊው ሕዝብ እንደ መስጂድ ግልጋሎት ላይ የዋለው በአብርሃም እና በልጁ መሰረቱ ከፍ ተደርጎ ከተገነባና አብረሃም ሰዎችን ሁሉ ለሐጅ ስርዓት ወደዚያ ስፍራ ከጠራቸው ቡኋለ ነበር (ሱራ 22:27)። አንዳንድ አጉል ተከራካሪ ሰባኪዎች ‟በታሪክ ከአምስተኛው ክፍለዘመን በፊት መካ ውስጥ አይደለም ቤተመቅደስ ሊኖር ይቅርና ጭራሽ መካ የምትባል ከተማ ራሱ በዐረብ ምድር አትታወቅም” ብለው ያለ እውቀት ይናገራሉ። አለማንበብ ብዙ ያስወራል ! ለማንኛውም ከታሪክ መዛግብት ከዕባ አይደለም ከ5ኛ ክፍለዘመን በፊት ከክርስትና እድሜ ራሱ እንደሚቀድምና ስፍራውም የአምልኮ ቦታ መሆኑን ከጥንታዊያን የታሪክ ጸሐፊዎች መረዳት እንችላለን።
የአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለዘመን የታሪክ ምሁር የሆነው እንግሊዛዊው ኤድዋርድ ጊበን በ60 BC አከባቢ (ቅደመ ክርስቶስ) የነበረውን ግሪካዊውን የታሪክ ጸሐፊ ዳዮዶሩስን (Diodorus Siculus) በመጥቀስ ስለ ከዕባ ጥንታዊነት እንዲህ በማለት ይናገራል:- ❝የከዕባ ትክክለኛ (እውነተኛ) ጥንታዊነት ከክርስትናው ዘመን ይቀድማል። የግሪክ የታሪክ ጸሐፊ የሆነው ዲዮዶሩስ የቀይ ባሕርን ዳርቻ በሚገልጽበት ጊዜ በሰሙዳዊያን (Thamudites) እና ሳባዊያን (Sabeans) መካከል በሁሉም ዐረቦች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታዋቂ ቤተ-መቅደስ መኖሩን ገልጿል…ይህ በቱርክ ንጉሰ-ንግሥት በየዓመቱ በሐር የሚታደሰው (መቅደስ) ከመሐመድ ዘመን በፊት ሰባት መቶ ዓመታት አስቀድሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በHomerit’ቶች ይቀርብ (ይታደስ) ነበር❞
(📘Gibbon’s Decline And Fall Of The Roman Empire, Volume V, Everyman’s Library, London, pp. 223-224.)
ይህ ቅድመ-ክርስቶስ የነበረው ግሪካዊው የታሪክ ጸሐፊ “Bibliotheca Historica” ለተሰኘው መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን ስለ ቤተመቅደሱ እንዲህ በማለት ነበር የጻፈው:- ‟And a temple has been set-up there, which is very holy and exceedingly revered by all Arabians” ትርጉም:- ❝በዚያች ስፍራ ላይም በሁሉም ዐረቦች ዘንድ እጅግ የተቀደሰ እና የከበረ ቤተመቅደስ ተገነባ❞
(📜Diodorus Of Sicily, Translated by C H Oldfather, Vol II, p.217)
እንደምንመለከተው ይህ ቅደመ-ኢየሱስ በፊት የነበረው የታሪክ ጸሐፊ በዐረብ ምድር አረቦች በዚያች አከባቢ እንደሚኖሩ እና ቤተመቅደስ ለሆነው ከዕባ ከፍተኛ ቦታ እንደነበራቸው ይዘክራል። ይህም የመካንና ከዕባን ጥንታዊነት ከሚያሳዩ የታሪክ መዛግብት ውስጥ አንዱ ሲሆን ሌሎችም እጅግ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ለምሳሌ ክላውዲዮስ ፓትሎሚ (90 AD) የተባለው የስነ-ፈለክ ተመራማሪ እና ጂኦግራፈር ዐረቢያንና በዙርያዋ የሚገኙ ሀገራትን በሚጽፍበት የዓለም ካርታ ዝርዝሩ ላይ፣ ስለ አረብ ምድር ሲገልጽ “መካን” በስም “Macoraba” በማለት ይጠቅሳታል (Arabia Felix Map, Book 6, Chapter VII, Sixth map of Asia)
‟መኮራባ” Μακοράβα ማለት “የጌታ ቤት” (House of Lord) ማለት ሲሆን በጥንት ዘመን መካን ለመጥራት የሚጠቀሙበት ስም መሆኑን የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ይገልጻሉ። ለምሳሌ የ19ኛው መቶ ክፍለዘመን የቃላት ሊቅ (Lexicographer) የሆነው ዊልያም ስሚዝ እንዲህ በማለት ይናገራል ❝MACORABA is, an inland city of Arabia, placed by Ptolemy universally admitted to be the ancient classical representative of the modern Mekka // መኮራባ በ ፕቶለሚ የተዘከረች የአረብ ከተማ ስትሆን በአለማቀፍ ደረጃ ዘመናዊዋ “መካ” እንደሆነች ይታመናል።❞
(Dictionary of Greek and Roman Geography (1854) William Smith, LLD, Ed)
አሁንም “Gustave E. von” የተባለው ኦስትሪያዊ የታሪክ ተመራማሪ በ ፖትለሚ የተጠቀሰችው የአረብ ከተማ መካ ስለመሆኗ እንዲህ በማለት ይገልፃል ❝Mecca is mentioned by Ptolemy, and the name he gives it allows us to identify it as a South Arabian foundation created around a sanctuary / መካ በፖትለሚ የተጠቀሰች ከተማ ስትሆን እርሱ የሰየመበት ስም በደቡብ አረቢያ በመቅደሱ ዙርያ የተፈጠሩ (አረቦች) መኖራቸውን እንድንለይ ያስችለናል።❞
(G E Von Grunebaum, Classical Islam: A History 600-1258, George Allen & Unwin Limited, 1970, p.19)
በቄርሎስ ግላሲ የተጻፈው የኢስላም መድብለ-እውቀት (The New Encyclopedia of Islam) ላይ ፖትለሚ የጠቀሰው ከተማ በትክክል የዛሬዋ መካ መሆኗን እንዲህ በማለት ያብራራል:- ❝For thousands of years Mecca has been a spiritual center. Ptolemy, the second century Greek geographer, mentioned Mecca, calling it ‘Makoraba / ለብዙ ሺ ዓመታት መካ መንፈሳዊ ማዕከል ሆና ቆይታለች። የሁለተኛው ክፍለዘመን የግሪክ ጂኦግረፈር የሆነው ፖቶለሚ መካን “መኮራበ” በማለት ይጠቅሳታል።❞
(The New Encyclopedia of Islam by Cyril Glasse page 302)
ኢልያ ፓቭሎቪች (1898 – 1977) በሌኒንግራድ ዩኒቨርሲቲ የምስራቅ ታሪክ ፕሮፌሰር ሲሆኑ በሁለተኛው ክፍለዘመን በግሪኩ የስነ-ፈለክ ተመራማሪ የተጠቀሰችው ከተማ የአሁኗ መካ መሆኗን በአጽንኦት ይዘክራሉ ❝The Greek geographer, mentions (mecca) it as early as the second century calling it Makoraba, which is derived from the south Arab word Maqrab meaning ‘sanctuary❞
(Islam in Iran by I. Pavlovich Petrushevsky page 3)
በተመሳሳይ ሚካኤል ዋልፍ የተባለው ጸሐፊ በርዕሱ ላይ እንዲህ በማለት ይናገራል ❝መካ በአረቢያ ምዕራባዊ የባህር ጠረፍ መሃሉ አከባቢ በተለምዶ ሒጃዝ በሚባል ተራራማ ድንበር የምትገኝ ከተማ ናት። የሁለተኛው መቶ ክፍለዘመን የግሪኮ-ግብፃዊ ጂኦግራፈር ፖቶለሚ መኮራበ ቤተመቅደስ ብሎ ይጠራታል❞
(One Thousand Roads to Mecca… by Michael Wolfe introduction xv)
ፕሮፌሰር ጳውሎስ (Paul Wheatley) PhD:- የተባለው የታሪክ ምሁር በፖቶለሚ የተጠቀሰችውን ከተማ በተመለከ እርሱም በበከሉ እንዲህ ሲል ይናገራል:- ❝The name Mecca (strictly transliterated as Makkah) had been mentioned in the Ptolmaic corpus in the 2nd century AD under the orthography Makoraba, which itself derived from the Sabaean Makuraba, meaning ‘sanctuary / መካ የሚለው ስም (ሲጠብቅ መካህ ተብሎ ይነበባል) በ2ኛው መቶ ክፍለዘመን በፕቶለሚ ኮርፐስ (ካርታ) ውስጥ መኮራባ በሚለው የፊደል አጻጻፍ ስር ተጠቅሶ ይገኛል። ይህም ከሳባውያን ማኩራባ የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ‟መቅደስ“ ማለት ነው።
(Paul Wheatley The Origins and Character of the Ancient Chinese City: volume 11 page 288)
ማጠቃለያ:- መካ ሚሺነሪዎች እንደሚቀጥፉት ከአምስተኛ ክፍለዘመን ቡኋለ የተፈጠረች ከተማ ሳትሆን በጥንት ዘመን ቅድመ-ክርስቶስ እንኳን በታሪክ-ጸሐፊያን የምትታወቅ ቅዱስ ከተማ ናት። በዚያ የሚገኘው የከዕባ ቤተመቅደስም እድሜ ጠገብ የሆነ በጥንታዊያን ሕዝቦች የሚታወቅ ቤተ-አምልኮ መሆኑን ከላይ ተመልክተናል። የሰባኪያኑ ሙግት ከመረጃ-መጉደል እና አለማጣረት የመጣ ወሬ መሆኑን በቀላሉ መረዳት እንችላለን። ፈጣሪ ልቦና ይስጣቸው እንጂ ሌላ ምን ይባላል?
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


