ኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
1/ በአላህ አንድነት፣ በነቢዩ ሙሐመድ ነቢይነት፣ በኢስላም ሃይማኖትነት ያመነች ሙስሊም ሴት በምንም አይነት መልኩ እርኩስ አይደለችም። ርክሰት የከሀዲያን መገለጫ ነው። ሙሽሪኮች ጣኦት አምላኪ በመሆናቸው ርኩሳን ናቸው። የአላህ ቃል እንዲህ ይላል:–
“يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا إِنَّمَا الْمُشْرِكُونَ نَجَسٌ…” سورة التوبة 28
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አጋሪዎች እርኩሶች ብቻ ናቸው …” (ሱረቱ–ተውባህ 9:28)።
በአንድ የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ ላይ የቀረበን የወገኖቻችንን የተንሸዋረረ ግንዛቤ በማቅረብ: ትክክለኛ እርምቱን በመጠኑ ለማቅረብ እሞክራለሁ ኢንሻአላህ።
” وَيَسْأَلُونَكَ عَنِ الْمَحِيضِ قُلْ هُوَ أَذًى فَاعْتَزِلُوا النِّسَاءَ فِي الْمَحِيضِ وَلَا تَقْرَبُوهُنَّ حَتَّى يَطْهُرْنَ فَإِذَا تَطَهَّرْنَ فَأْتُوهُنَّ مِنْ حَيْثُ أَمَرَكُمُ اللَّهُ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ التَّوَّابِينَ وَيُحِبُّ الْمُتَطَهِّرِينَ ” سورة البقرة 222
“ከወር አበባም ይጠይቁሃል፡፡ እርሱ አስጠያፊ ነው፡፡ ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው፡፡ ንጹሕ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቡዋቸው፡፡ ንጹሕ በኾኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኙዋቸው፡፡ አላህ (ከኃጢኣት) ተመላሾችን ይወዳል፤ ተጥራሪዎችንም ይወዳል በላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 222)፡፡
በዚህ አንቀፅ ውስጥ “ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው፡፡ ንጹሕ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቡዋቸው” የሚለውን ቃል በመምዘዝ: ሴቶችን ራቁ የተባለው እርኩስ ስለሆኑ ነው ይሉናል። የኛ ምላሽም:–
1ኛ/ በአንቀጹ ውስጥ ‹‹ሴቶችን ራቋቸው›› እና ‹‹አትቅረቧቸው›› ተብለው የተጠቀሱት ቃላቶች: የሚያመለክቱት የግብረ–ስጋ ግኑኙነት ከመፈፀም መከልከል እንዳለብን እንጂ: ሴቶች እርኩስ መሆናቸውን አይደለም። በወር አበባ ወቅት ከትዳር አጋር ጋር ግኑኝነት መፈፀም ክልክል መሆኑን ለመግለፅ ነው “ራቋቸው” እና “አትቅረቧቸው” የተባለው። ይህንን የቁርኣን ክፍል የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ራሳቸው እንዲህ በማለት አብራርተውታል፡-
عَنْ أَنَسٍ أَنَّ الْيَهُودَ كَانُوا إِذَا حَاضَتِ الْمَرْأَةُ فِيهِمْ لَمْ يُؤَاكِلُوهَا، وَلَمْ يُجَامِعُوهُنَّ فِي الْبُيُوتِ فَسَأَلَ أَصْحَابُ النَّبِيِّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ النَّبِيَّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ فَأَنْزَلَ اللهُ تَعَالَى {وَيَسْأَلُونَكَ عَنِ الْمَحِيضِ قُلْ هُوَ أَذًى فَاعْتَزِلُوا النِّسَاءَ فِي الْمَحِيضِ} [البقرة: 222] إِلَى آخِرِ الْآيَةِ، فَقَالَ رَسُولُ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: «اصْنَعُوا كُلَّ شَيْءٍ إِلَّا النِّكَاحَ» فَبَلَغَ ذَلِكَ الْيَهُودَ، فَقَالُوا: مَا يُرِيدُ هَذَا الرَّجُلُ أَنْ يَدَعَ مِنْ أَمْرِنَا شَيْئًا إِلَّا خَالَفَنَا فِيهِ،…” رواه المسلم.
አነስ ኢብኑ-ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አለ፡- “አይሁዶች ሚስቶቻቸው ሐይድ ላይ ሲሆኑ፡ አብረዋቸው አይመገቡም፣ በቤት ውስጥም አብረዋቸው አይተኙም ነበር፡፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሶሐባዎችም ስለ ጉዳዩ ጠየቁ፡፡ ከዛም ከላይ የተጠቀሰው የቁርኣን አንቀጽ ወረደ፡፡ የአላህ መልክተኛም፡- ‹‹ከግብረ-ስጋ ግንኙነት በስተቀር ሁሉንም አድርጉ›› በማለት መለሱ፡፡ ይህ ነገርም አይሁዶች ዘንድ ደረሰ፡፡ እነሱም፡- ይህ ሰው (ታላቁን ነቢይ) ከጉዳያችን ላይ ቢቃረነን እንጂ ምንም አልተወም አሉ፡፡” (ሙስሊም )፡፡ Muslim :: Book 3 : Hadith 592
2ኛ/ “ሴቶችን በወር አበባ ወቅት ራቋቸው!” የሚለው አምላካዊ መመሪያ: የግብረ–ስጋ ግኑኙነት ከመፈፀም ብቻ እንጂ ከሌላ ነገር አለመሆኑን የሚያሳየን ሌላው ነገር: የመልክተኛው ተግባር ነው። ነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር በወር አበባ ወቅት እነዚህን ነገራት ይፈፅሙ ነበር:–
ሀ. አብሮ መተኛት፡-
እናታችን መይሙናህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- ‹‹የአላህ መልክተኛ እኔ በሐይድ ላይ እያለሁ በሳቸውና በእኔ መሐከል ልብስ ይደረግና አብረውኝ ይተኙ ነበር›› (ሙስሊም)፡፡ Muslim :: Book 3 : Hadith 580 ።
ለ. አብሮ መብላት፡-
እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- ‹‹እኔ በሐይድ ላይ ሁኜ ሳለ በእቃ እጠጣና ከዛም የጠጣሁበትን እቃ ለአላህ መልክተኛ እሰጣቸውና፡ አፋቸውን እኔ በጠጣሁበት ቦታ በማድረግ ይጠጡበት ነበር፡፡ በወር አበባ ላይ ሁኜ አጥንትንም (ስጋ ያለውን) እመገብ ነበር፡፡ ከዛም ለሳቸው እሰጣቸውና እሳቸውም የኔ አፍ የነካበት ቦታ ላይ አፋቸውን ያደርጉበት ነበር›› (ሙስሊም)፡፡Muslim :: Book 3 : Hadith 590።
ሐ. መታጠብና ጸጉርን ማበጠር
እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- ‹‹እኔ በሐይድ ላይ ሳለሁ የአላህ ነቢይም (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ይነኩኝ ነበር፡፡ በመስጂድ ውስጥም ኢዕቲካፍ አድርገው ሳለ፡ ከመስጂዱ ራሳቸውን ወደ ውጭ ያወጡና እኔ አጥባቸው ነበር›› (ቡኻሪና ሙስሊም) Bukhari :: Book 3 :: Volume 33 :: Hadith 247
አሁንም በድጋሚ እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ ትላለች፡- ‹‹እኔ በሐይድ ወቅት ሆኜ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በመስጂድ ውስጥ ሆነው ራሳቸውን ወደኔ ያስጠጉትና ጸጉራቸውን አበጥርላቸው ነበር፡፡›› (ቡኻሪና ሙስሊም ) Bukhari :: Book 3 :: Volume 33 :: Hadith 245
ይህ ነበር የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አስተምህሮትና ሞዴል!!፡፡ ሴት ልጅ በወር አበባ ወቅት የሚፈሳት ደም ነው እንጂ ቆሻሻ: እሷ ቆሻሻ አይደለችም። እሷ እርኩስ ብትሆን ኖሮማ አብሮ መብላቱና መጠጣቱ: አብሮ ማደሩም መች ይኖር ነበር?
3ኛ/ ከቅዱስ ቁርኣን ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ገለፃ ሴትን ልጅ በእጅጉ አርክሷታል። መጽሐፍ ቅዱስ የወር አበባን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:–
“ሴት ፈሳሽ ነገር ቢኖርባት በሥጋዋም ያለው ፈሳሽ ነገር ደም ቢሆን፥ በመርገምዋ ሰባት ቀን ትቀመጣለች፤ የሚነካትም ሁሉ እስከ ማታ ድረስ #ርኩስ ነው። 20፤ መርገምም ስትሆን የምትተኛበት ነገር ሁሉ #ርኩስ ነው፤ የምትቀመጥበትም ነገር ሁሉ #ርኩስ ነው። 21፤ መኝታዋንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ #ርኩስ ነው። 22፤ የምትቀመጥበትንም ነገር ሁሉ የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም #ርኩስ ነው። 23፤ በመኝታዋም ላይ ወይም በምትቀመጥበት ነገር ላይ ቢሆን ሲነካው እስከ ማታ ድረስ #ርኩስ ነው። 24፤ ማንም ከእርስዋ ጋር ቢተኛ መርገምዋም ቢነካው፥ ሰባት ቀን #ርኩስ ነው፤ የሚተኛበትም መኝታ ሁሉ #ርኩስ ነው። 25፤ ሴትም ከመርገም ቀን ሌላ ደምዋ ብዙ ቀን ቢፈስስ፥ ወይም ደምዋ ከመርገምዋ ወራት የሚበልጥ ቢፈስስ፥ በመርገምዋ ወራት እንደ ሆነች እንዲሁ በፈሳሽዋ ርኵስነት ወራት ትሆናለች፤ #ርኩስ ናት። 26፤ ደምዋም በሚፈስስበት ወራት ሁሉ የምትተኛበት መኝታ ሁሉ በመርገምዋ ጊዜ እንደ ነበረው መኝታ ያለ ይሆንባታል፤ የምትቀመጥበት ነገር ሁሉ እንደ መርገምዋ ርኵስነት #ርኵስ ነው። 27፤ እነዚህንም ነገሮች የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ልብሱንም ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም #ርኩስ ነው። 28፤ ከፈሳሽዋም ብትነጻ ሰባት ቀን ትቈጥራለች ከዚያም በኋላ ንጹሕ ትሆናለች። 29፤ በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዛ ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ታመጣቸዋለች። 30፤ ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም ስለ ፈሳሽዋ #ርኵስነት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል።”
(ኦሪት ዘሌዋውያን ምእ15፡ ቁ 19-30)፡፡
ወገኖች ሆይ! ይኸው መመሪያችሁ! ምነው ሴት ልጅ ይህን ያህል እንደ እንደ እቃ የረከሰች ናትን? ባለቤቷ ወደሷ መቅረብ የሚችለው ንጹህ ስትሆን ብቻ ነውን? በጣም የሚገርመው ደግሞ የሷ መርከስ ብቻ ሳይሆን እሷ የነካችው፣ ያረፈችበት፣ እሷንም የነካት ማንኛውም ነገር የረከሰ መሆኑ ነው፡፡ እንዴት ነው ታዲያ ቤተሰባዊ ህይወት መምራት የሚቻለው?
-አቶ ባል ከስራ ስትመጣ ባለቤትህን እንኳን ልትስማት፡ ከነካሀት ራሱ ትረክሳለህ፡፡ እሷ የነካችውን የምትነካም ከሆነ ትረክሳለህ፡፡ መርከስም ብቻ አይደለም ልብስህንና ገላህን ትታጠባለህ፡፡ ታጥበህም አይወርድልህ እስኪመሽም ድረስ ረክሰህ ትውላለህ፡፡
እሷ ባረፈችበት ወንበርም ሆነ መኝታ ላይ አርፋለሁ ብትል አሁንም ትረክሳለህ፡፡ ገላህን ታታጠባለህ ልብስህንም ታጥባለህ፡፡ አብረሀት ከተኛህና ከርክሰትዋ ቢነካህ አንተም አብረህ ሰባት ቀን የረከስክ ትሆናለህ፡፡ አጂብ!፡፡ ታዲያ ሴት እህቶቼ አላህ ሙስሊም ስላደረጋችሁ አልሐምዱ ሊላህ አትሉም?
አዎ! አልሐምዱ ሊላህ፡፡ ኢስላም እንደዚህ አላስተማረንም፡፡ በወር አበባ ወቅት አንድ ባል ከሚስቱ የተከለከለው ነገር አንድና አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እሱም ግብረ-ስጋ ግኑኝነት! በቃ ይሄ ነው፡፡ ከዛ ውጪ አብሯት ቢቀመጥ፣ ቢጫወታት፣ ቢያጎርሳት፣ ቢያቅፋትና ቢስማት፣ በአንድ መኝታም አብሯት ቢተኛ አልተከለከለም፡፡
በጣም ከገረሙኝ የመጽሐፍ ቁዱስ የወር አበባ ፍርድ ላይ ‹‹ማንም ከእርስዋ ጋር ቢተኛ መርገምዋም ቢነካው፥ ሰባት ቀን #ርኩስ ነው›› የሚለው ነው፡፡ ከዚህ የወር አበባ ደም ነካው ተብሎ ሰባት ቀን ሙሉ የሚረክስ ባል!!፡፡ ታዲያ ምኑ ገረመህ? ካላችሁኝም፡ የአላህ መልክተኛም ይህ ነገር ገጥሟቸው ነበር፡፡ ታዲያ ምን ሆኑ? ካላችሁኝ ቀጣዩን ሐዲሥ አብረን እንከታተል፡-
እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- ‹‹እኔና የአላህ መልክተኛ በወር አበባ ላይ ሁኜ ሳለ በአንድ ልብስ (አንሶላ ወይም ሌላ) እንተኛ ነበር፡፡ ከኔ አንዳች ነገር (ከደሙ) ቢያገኛቸው፡ የነካውን ቦታ ያጥቡት ነበር፡፡ ወደሌላው ክፍልም (ለማጠብ) አያሰፉትም፡፡ ከዛም በዛው ልብስ (ገላ) ሶላትን ይሰግዱ ነበር›› (አቡ ዳዉድ 269) Dawud :: Book 1 : Hadith 269
ይህ ነው አርአያነት! ደሙ የነካውን የሰውነትም ሆነ የልብስ ክፍል በማጠብ መብቃቃት፡፡ የምን ሰባት ቀን መርከስ? ልብሱን ከሆነ የነካው የምን ገላ መታጠብ? ገላቸውን ከሆነ የነካው የምን ልብስ ማጠብ? ደግሞም ልብሱም ሆነ ገላው ሲታጠብ ደሙ የነካው ቦታ ላይ ብቻ ነው፡፡
ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ ሴቷ ከወር አበባዋ በነጻች ጊዜ (በስምንተኛው ቀን) የኃጢአት ማስተሰረያ የሚሆን መስዋእት እንድታቀርብ መታዘዟ ነው፡፡ ‹‹ካህኑም ስለ ፈሳሽዋ #ርኵስነት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል›› በማለት የወር አበባ ማየቷንም እንደ ኃጢአት መመልከቱና ከደሟ በነጻች ግዜ ለመስዋእትነት የሚሆን ነገር እንድታቀርብ ማዘዙ እጅጉኑ አስገራሚ ነው፡፡ የወር አበባ: አላህ በአደም ልጆች (ሴቶች) ላይ የወሰነው ተፈጥሮአዊ ፍርድ እንጂ የኃጢአት ውጤት አይደለም፡፡ ማን በሰራው ኃጢአት ማን ይረገማል?
ይህ የኦሪት ህግ ተሸሯል የምትሉ ወገኖች ካላችሁ ደግሞ በምትኩ የተተካውን አዲሱን ህግ አሳዩን፡፡ በባዶ ሜዳ ተሸሯል ማለት የትም አያደርስም፡፡ የሴት ልጅ ስብእና ይከበር!! እንደ እርኩስ መቆጠሯ ይብቃ!!
አምላካችን አላህ ሆይ! በኢስላም ላይ ጽናትን ለግሰን፡፡ በጨለማ ለሚመላለሱ ወገኖቻችንም ልባቸውን ለኢስላም ክፈተው፡፡ ዕውቀትንም ለግሰን፡፡ ከጠሞ አጥማሚዎችም በራሕመትህ ጠብቀን፡፡


