ኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
” وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ أَبَى وَاسْتَكْبَرَ وَكَانَ مِنَ الْكَافِرِينَ ” سورة البقرة 34
“ለመላእክትም «*ለአደም ስገዱ*» ባልን ጊዜ (አስታውስ) ፡፡ ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፤ ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፤ ኮራም ከከሓዲዎቹም ኾነ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡34)፡፡
” وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ قَالَ أَأَسْجُدُ لِمَنْ خَلَقْتَ طِينًا ” سورة الإسراء 61
“ለመላእክትም *ለአደም ስገዱ* ባልናቸው ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፡፡ «ከጭቃ ለፈጠርከው ሰው እሰግዳለሁን» አለ፡፡” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡61)፡፡
” وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ أَبَى ” سورة طه 116
“ለመላእክትም፣ *ለአዳም ስገዱ*፣ ባልን ጊዜ (አስታውስ)፤ ሰገዱም ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፣ እምቢ አለ።” (ሱረቱ ጣሀ 20፡116)፡፡
ለአብነት ያህል ባየናቸው በነዚህ ሶስት አንቀጾች መሰረት መላእክት በመላ (ዐለይሂሙ-ሰላም) እንዲሁም ኢብሊስ ለአባታችን አደም ዐለይሂ-ሰላም እንዲሰግዱ ታዘው ነበር፡፡ መላእክትም (ዐለይሂሙ-ሰላም) የጌታቸውን ትእዛዝ በመቀበል ለአደም (ዐለይሂ-ሰላም) ሰግደዋል፡፡ ኢብሊስ ግን በቅናትና በኩራት ስሜት አልሰግድም ብሎ ከጌታው ትእዛዝ አመጸ፡፡ በዚሁም ሰበብ ከፈረ (ከሀዲ ሆነ)፡፡
ይህ ስግደት ለአባታችን አደም (ዐለይሂ-ሰላም) ታላቅ ክብር ነው፡፡ በመላእክትና በጂንኒዎች (የኢብሊስ ዝርያዎች) ላይም ብልጫን የተጎናጸፈበት ነው፡፡ አንዳንድ ካፊር ወገኖች እዚህ ላይ የተቃውሞ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ እሱም፡- እንዴት አላህ ለአደም እንዲሰገድ ትእዛዝ ያስተላልፋል? ስግደት የሚገባው ለሱ ብቻ አይደለምን? ለሰው እንዲሰገድ ማዘዙ ክብሩን አሳልፎ መስጠት አይሆንምን? ኢብሊስስ እኔ ለፍጡር መስገድ የለብኝም! በማለቱ እንዴት ከጀነት ይባረራል? የሚል፡፡ እኛም ለዚህ ጥያቄ የሚኖረን ምላሽ፡-
1/ ከሁሉ በፊት ፈጣሪ አምላካችን አላህ ለሚሰራው ሥራ፣ ትእዛዝም ሰጠ ወይም ከለከለ፡ እንዴት እንዲህ ያደርጋል? ተብሎ የሚጠየቅ አምላክ አይደለም፡፡ እሱ ባሮቹን በሰጣቸው ኃላፊነት እንዴትና ለምን እንደሰሩ፡ እያንዳንዱን ነገር በማንሳት የሚጠይቅና የሚመረምር ጌታ እንጂ፡ እሱ በሚሰራውና በሚፈርደው ነገር ለምን ሰራ? ተብሎ የሚጠየቅ አይደለም፡፡ ይህ ከአምላካችን ጋር አደብ ማጣት ነው፡፡ በየትኛው ውስንና ደካማ አእምሮአችን ነው፡ የአእምሮ ፈጣሪ የሆነውን አላህ ሥራውን ልንመረምረው የምንችለው? የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” لَا يُسْأَلُ عَمَّا يَفْعَلُ وَهُمْ يُسْأَلُونَ ” سورة الأنبياء 23
“ከሚሠራው ሁሉ አይጠየቅም እነሱ (ፍጥረቶቹ) ግን ይጠየቃሉ።” (ሱረቱል አንቢያእ 21፡23)፡፡
2/ ለአደም የተከናወነው የመላእክት ስግደት የአክብሮት ስግደት እንጂ የአምልኮ ስግደት አልነበረም፡፡ የአላህንም መብት ለፍጡር አሳልፎ መስጠት አይሰኝም፡፡ ምክንያቱም ይህ የስግደት ትእዛዝ የመጣው ከራሱ ከአባታችን አደም (ዐለይሂ-ሰላም) አልነበረምና፡፡ ለኔ ስገዱልኝ! በማለት አላዘዘም፡፡ ወይንም መላእክት ለአደም እንስገድ ብለውም አልተማከሩም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ በርግጥም አምልኮ ይሆን ነበር፡፡ ግን አይደለም፡፡ ለአደም ስገዱ! የሚለው ትእዛዝ የመጣው ከጌታ አላህ መሆኑ፡ ጉዳዩ የአክብሮት እንጂ የአምልኮ አለመሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ መላእክት የፈጸሙት የአላህን ትእዛዝ ነውና፡ በተዘዋዋሪ አምልኮቱ ለአላህ ነው ማለት ነው፡፡
3/ ከአደም ዐለይሂ-ሰላም በኋላም ቢሆን የአክብሮት ስግደት በነቢያት ሸሪዓህ ውስጥ የተፈቀደ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ለአደም የነበረውንም ስግድት የአክብሮት እንጂ የአምልኮ አለመሆኑን ያጠናክረዋል፡፡ ነቢዩላህ ዩሱፍ (ዐለይሂ-ሰላም) በልጅነቱ ህልም አይቷል፡፡ ያየው ህልምም፡- አሥራ አንድ ከዋክብት፣ ፀሀይና ጨረቃ ለርሱ ሰጋጆች ሁነው ነው፡፡ ይህ ህልም ቅዠት አልነበረምና በመጨረሻም ጌታ አላህ እውን አደረገለት፡፡ እሱም ነቢይና ረሱል ሆኖ ከተመረጠ በኋላ፣ በሀገረ ግብፅ ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ ወንድሞቹንና ቤተሰቦቹን በአላህ ፈቃድ በማስመጣት በተገናኙት ጊዜ በኮኮብ ምስል የታዩት አሥራ አንዱ ወንድሞቹ፣ በጨረቃና በፀሀይ ምስል የታዩት እናቱና አባቱ ለሱ ሱጁድ ወርደዋል (ሰግደውለታል)፡፡ ይህ ስግደት ግን የአክብሮት እንጂ የአምልኮ አልነበረም፡፡ ዩሱፍ (ዐለይሂ-ሰላም) ነቢይ ነው፡፡ ነቢይ ወደራሱ አምልኮ ሰውን ይጣራል ተብሎ አይገመትም፡፡ አባቱም የዕቁብ (ዐለይሂ-ሰላም) ነቢይ ነው፡፡ ነቢይ ፍጡርን ያመልካል ተብሎም አይታሰብም፡፡ ቁርኣን እንዲህ ያስተምራል፡-
” إِذْ قَالَ يُوسُفُ لِأَبِيهِ يَا أَبَتِ إِنِّي رَأَيْتُ أَحَدَ عَشَرَ كَوْكَبًا وَالشَّمْسَ وَالْقَمَرَ رَأَيْتُهُمْ لِي سَاجِدِينَ….فَلَمَّا دَخَلُوا عَلَى يُوسُفَ آوَى إِلَيْهِ أَبَوَيْهِ وَقَالَ ادْخُلُوا مِصْرَ إِنْ شَاءَ اللَّهُ آمِنِينَ * وَرَفَعَ أَبَوَيْهِ عَلَى الْعَرْشِ وَخَرُّوا لَهُ سُجَّدًا وَقَالَ يَا أَبَتِ هَذَا تَأْوِيلُ رُؤْيَايَ مِنْ قَبْلُ قَدْ جَعَلَهَا رَبِّي حَقًّا وَقَدْ أَحْسَنَ بِي إِذْ أَخْرَجَنِي مِنَ السِّجْنِ وَجَاءَ بِكُمْ مِنَ الْبَدْوِ مِنْ بَعْدِ أَنْ نَزَغَ الشَّيْطَانُ بَيْنِي وَبَيْنَ إِخْوَتِي إِنَّ رَبِّي لَطِيفٌ لِمَا يَشَاءُ إِنَّهُ هُوَ الْعَلِيمُ الْحَكِيمُ ” سورة يوسف 4 و 100-99
“ዩሱፍ ለአባቱ፦ አባቴ ሆይ! እኔ ዐሥራ አንድ ክዋክብትን ፀሐይንና ጨረቃን (በሕልሜ) አየሁ፤ ለእኔ ሰጋጆች ሆነው አየኋቸው ባለ ጊዜ (አስታውስ)….በዩሱፍ ላይም በገቡ ጊዜ. ወላጆቹን ወደርሱ አስጠጋቸው፤ በአላህም ፈቃድ ጥብቆች ስትሆኑ ምስርን ግቡ፣ አላቸው።ወላጆቹንም በዙፋኑ ላይ አወጣቸው፤ ለርሱም ሰጋጆች ሆነው ወረዱለት፤ አባቴም ሆይ ይህ ፊት ያየኋት ሕልሜ ፍች ነው፤ ጌታዬ በእርግጥ እውነት አደረጋት፤ ከወህኒ ቤትም ባወጣኝና ሰይጣንም በኔና በወንድሞቼ መካከል ከአበላሸ በኋላ እናንተን ከገጠር ባመጣችሁ ጊዜ፣ በእርግጥ ለኔ መልካም ዋለልኝ፤ ጌታዬ ለሚሻው ነገር እዝነቱ ረቂቅ ነው፤ እነሆ እርሱ ዐዋቂው ጥበበኛው ነው፤ አለ።” (ሱረቱ ዩሱፍ 12፡4.99-100)፡፡
4/ ጠላታችን ኢብሊስ ለአደም (ዐለይሂ-ሰላም) ከመስገድ የታቀበው፡ ስግደት ለአንዱ አምላክ ለአላህ የተገባ ነው! ብሎ ለጌታው ክብር ስለቀና ሳይሆን፡ ለበታቼ አልሰግድም! ከሚል የምቀኝነትና የጥላቻ ስሜት በመነሳት ነው፡፡ አደምን ከራሱ አሳንሶ ነበር የተመለከተው፡፡ እሱ ከእሳት መፈጠሩን በመጥቀስ፡ ከጭቃ ከተፈጠረው አደም በላጭ ነኝ! ብሎ በማሰብ እንቢ አለ እንጂ፡ መች ለጌታው ክብር ቀና? ለጌታው ክብር የሚቀና ቢሆን ኖሮ ትእዛዙንም ባከበረ ነበር፡፡ የአላህ ቃል ግን እንዲህ ይላል፡-
” قَالَ مَا مَنَعَكَ أَلَّا تَسْجُدَ إِذْ أَمَرْتُكَ قَالَ أَنَا خَيْرٌ مِنْهُ خَلَقْتَنِي مِنْ نَارٍ وَخَلَقْتَهُ مِنْ طِينٍ ” سورة الأعراف 12
“(አላህ) ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ? አለው፤ እኔ ከርሱ የበለጥኩ ነኝ፤ ከእሳት ፈጠርከኝ፤ እሱን ግን ከጭቃ ፈጠርከው አለ።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡12)፡፡
” قَالَ يَا إِبْلِيسُ مَا لَكَ أَلَّا تَكُونَ مَعَ السَّاجِدِينَ (32) قَالَ لَمْ أَكُنْ لِأَسْجُدَ لِبَشَرٍ خَلَقْتَهُ مِنْ صَلْصَالٍ مِنْ حَمَإٍ مَسْنُونٍ ” سورة الحجر 33-32
“(አላህም) «ኢብሊስ ሆይ! ከሰጋጆቹ ጋር የማትኾን ላንተ ምን ምክንያት አለህ» አለው፡፡«ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከግም ጭቃ ለፈጠርከው ሰው ልሰግድ አይገባኝም» አለ፡፡” (ሱረቱል ሒጅር 15፡32-33)፡፡
” وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ قَالَ أَأَسْجُدُ لِمَنْ خَلَقْتَ طِينًا ” سورة الإسراء 61
“ለመላእክትም ለአደም ስገዱ ባልናቸው ጊዜ (አስታውስ)፡፡ ወዲያውም ሰገዱ፤ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፡፡ «ከጭቃ ለፈጠርከው ሰው እሰግዳለሁን» አለ፡፡” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡61)፡፡
5/ በዚህ ለአደም ስገዱ! በሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ አማካኝነት የኢብሊስ ውስጣዊ ማንነቱ ተጋለጠ፡፡ ፈተናውንም ወደቀ፡፡ አላህ አደምን (ሰውን) ብልጫና ክብር ስለሰጠው፡ እንዴት በኔ ላይ ሰው ይሾምብኛል በማለት ገና ከፍጥረቱ ማግስት ጀምሮ በውስጡ ቂምን የቋጠረው ኢብሊስ፡ መላእክት ለአደም የአክብሮት ስግደትን የታዘዙ ጊዜ፡ እሱም ታዘዘ፡፡ የዛኔ ውስጠዊ ማንነቱ ተገለጠ፡፡ ቅናቱና ምቀኝነቱ ወደ ክህደት ገፋፋው፡፡ የጌታውንም ትእዛዝ በማመጽ ካደ፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” قَالَ أَرَأَيْتَكَ هَذَا الَّذِي كَرَّمْتَ عَلَيَّ لَئِنْ أَخَّرْتَنِ إِلَى يَوْمِ الْقِيَامَةِ لَأَحْتَنِكَنَّ ذُرِّيَّتَهُ إِلَّا قَلِيلًا… ” سورة الإسراء 62
“ንገረኝ ይህ ያ በኔ ላይ ያበለጥከው ነውን? እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ ብታቆየኝ ዘሮቹን ጥቂቶች ሲቀሩ ወደ ስሕተት በእርግጥ እስባቸዋለሁ አለ።” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡62)፡፡
ይህ ነበር በሽታው! እንዴት አደም በኔ ላይ ብልጫ ይሰጠዋል! እንዲት እሱና ዝርያዎቹ በምድር ላይ ኸሊፋህ (ምትክ) ይሆናሉ! እኮ እንዴት! የሚል በሽታ፡፡ (ወል-ዒያዙ ቢላሂ ሚነል ሐሰድ!)፡፡
6/ የአክብሮት ስግደት ሐራም የተደረገው በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሸሪዓ ነው፡፡ በቅዱስ ቁርኣንና በሐዲሥ ሕይወቱን የሚመራ ሙስሊም ለማንኛውም አካል (ለወላጅ፣ ለሃይማኖት መሪዎች፣ ለመንግስት ባለ-ስልጣናት…) የአክብሮትን ስግደት መስገድ አይችልም!፡፡ ይህን ካደረገ ኃጢአኛ ሆኖ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡ ማስረጃውም ቀጣዩ ነቢያዊ ሐዲሥ ነው፡-
فعَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ أَبِي أَوْفَى ، قَالَ : ” لَمَّا قَدِمَ مُعَاذٌ مِنَ الشَّامِ سَجَدَ لِلنَّبِيِّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ، قَالَ: ( مَا هَذَا يَا مُعَاذُ؟ ) ، قَالَ : أَتَيْتُ الشَّامَ فَوَافَقْتُهُمْ يَسْجُدُونَ لِأَسَاقِفَتِهِمْ وَبَطَارِقَتِهِمْ ، فَوَدِدْتُ فِي نَفْسِي أَنْ نَفْعَلَ ذَلِكَ بِكَ ، فَقَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: ( فَلَا تَفْعَلُوا، فَإِنِّي لَوْ كُنْتُ آمِرًا أَحَدًا أَنْ يَسْجُدَ لِغَيْرِ اللَّهِ ، لَأَمَرْتُ الْمَرْأَةَ أَنْ تَسْجُدَ لِزَوْجِهَا، وَالَّذِي نَفْسُ مُحَمَّدٍ بِيَدِهِ، لَا تُؤَدِّي الْمَرْأَةُ حَقَّ رَبِّهَا حَتَّى تُؤَدِّيَ حَقَّ زَوْجِهَا) رواه ابن ماجه (1853) وحسنه الألباني.
ዐብዲላህ ኢብኒ አቢ ዐውፋ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- ሙዓዝ ኢብኑ ጀበል (ረዲየላሁ ዐንሁ) ከሻም (ሶሪያ) ምድር በተመለሰ ጊዜ ለነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሰገደ (ሱጁድ ወረደ)፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹ሙዓዝ ሆይ! ምንድነው ይህ?›› አሉት፡፡ እሱም፡- ‹‹ሻም ምድር ሄጄ ነበር፡፡ ለጳጳሳቶቻቸውና ለፓትሪያርኮቻቸው ሲሰግዱ ተመለከትኩኝ፡፡ በውስጤም ይህን ነገር (የአክብሮት ስግደት) ለርሶ ልንሰራው በውስጤ ተመኘሁ›› አለ፡፡ የአላህ መልክተኛም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም)፡- ‹‹ይህንን በፍጹም እንዳትሰሩ! እኔ ከአላህ ውጪ ስግደትን ለሰው የማዝ ብሆን ኖሮ፡ ሚስትን ለባሏ እንድትሰግድ አዛት ነበር፡፡ ነፍሴ በእጁ በሆነው አላህ እምላለሁ፡፡ ሚስት የባሏን ሐቅ (መብት) እስክትወጣ ድረስ የጌታዋን የአላህ ሐቅ አትወጣምና›› በማለት ከለከሉት፡፡ (ኢብኑ ማጀህ 1853)፡፡
ለማጠቃለል ያህል፡- ለአባታችን አደም (ዐለይሂ-ሰላም) የነበረው የመላእክት ስግደት፡ የአክብሮት እንጂ የአምልኮ አልነበረም፡፡ አይደለምም፡፡ ሊሆንም አይችልም!! የኢብሊስም እንቢተኝነት ትእቢትና ቅናት የወለደው እንጂ፡ ስግደት ለአላህ ብቻ የሚገባ መለኮታዊ መብቱ መሆኑን በማወቅ ለጌታው መቅናቱ አልነበረም፡፡ መጽሐፍትን በአግባቡ አንብበው ሳይረዱ ለመቃወም አይቸኩሉ!!
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


