ኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
በየትኛው ስነ-አመክንዮ ነው ይህ ሀሳብ እውነት መሆን የሚችለው? እውነት ኃጢአትን ከኃጢአተኛው ለይቶ መግለጽ ይቻላልን? ኃጢአተኛው ጻድቅ ቢሆን ኖሮ ኃጢአት ትርጉም እና ምንነት ይኖረው ነበርን? አምላክስ ኃጢአተኛውን ከወደደው፡ ጀሀነም እሳትን ያዘጋጀው ለጻድቃን ነው ማለት ነውን? ወይስ ኃጢአት እራሱ አካል ለብሶ ወደ ጀሀነም እሳት ይወረወራል? መቼም አምላክ የሚወደውን ኃጢአተኛ ባሪያውን በጀሀነም እሳት ያሰቃየዋል የሚል አስተምህሮ አይኖርም፡፡ ካለም ስህተት እንጂ እውነት መሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ጀሀነም እሳት የአምላክ ቁጣ መገለጫ የሆነ የቅጣት ስፍራ እንጂ፡ የፍቅሩ መገለጫ የሆነ የወዳጆቹ የክብር ስፍራ አይደለም፡፡ ታዲያ ገሀነም የተዘጋጀው ለኃጢአተኞች ከሆነ፡ አምላክ ኃጢአተኛን ቢወደው ነው ቢጠላው ጀሀነምን የደገሰለት? አእምሮ የተሰጠን ምን ልናደርግበት ነው? ገና ህፃን ሳለ ጭንቅላት የተፈጠረው ለምንድነው? ብዬ ስጠይቀው፡ ኮፍያ ለማስቀመጥ በማለት የመለሰልኝ ልጄ ሐይደር ለካ እውነቱን ነበር!!
የአላህ ቃል የሆነው ቅዱስ ቁርኣን አላህ ከኃጢአታቸው በተውበት/ንሰሀ የሚመለሱ ባሮቹን እንደሚወድ እንጂ፡ በኃጢአት ባሕር የተዘፈቁና የዋኙ ባሮቹን እንደሚወድ አያስተምረንም፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” وَيَسْأَلُونَكَ عَنِ الْمَحِيضِ قُلْ هُوَ أَذًى فَاعْتَزِلُوا النِّسَاءَ فِي الْمَحِيضِ وَلَا تَقْرَبُوهُنَّ حَتَّى يَطْهُرْنَ فَإِذَا تَطَهَّرْنَ فَأْتُوهُنَّ مِنْ حَيْثُ أَمَرَكُمُ اللَّهُ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ التَّوَّابِينَ وَيُحِبُّ الْمُتَطَهِّرِينَ ” سورة البقرة 222
“ከወር አበባም ይጠይቁሃል፡፡ እርሱ አስጠያፊ ነው፡፡ ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው፡፡ ንጹሕ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቡዋቸው፡፡ ንጹሕ በኾኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኙዋቸው፡፡ አላህ (ከኃጢኣት) ተመላሾችን ይወዳል፤ ተጥራሪዎችንም ይወዳል በላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡222)፡፡
በተለይ አምላካችን አላህ ወደሱ በተውበት የሚመለሱትን፡ የኃጢአት ይቅርታን የሚጠይቁትን ባሪያዎች በጣም እንደሚወድ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ-ወሰለም) እንዲህ ሲሉ በምሣሌ ገልጸውታል፡-
عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، قَالَ: قَالَ رَسُولُ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: «وَالَّذِي نَفْسِي بِيَدِهِ لَوْ لَمْ تُذْنِبُوا لَذَهَبَ اللهُ بِكُمْ، وَلَجَاءَ بِقَوْمٍ يُذْنِبُونَ، فَيَسْتَغْفِرُونَ اللهَ فَيَغْفِرُ لَهُمْ»رواه مسلم 2749.
ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ነፍሴ በእጁ በሆነው አላህ ይሁንብኝ! እናንተ ኃጢአትን ባትሰሩ ኖሮ፡ አላህ ያጠፋችሁና፡ ኃጢአትን ሰርተው ከዛም ጌታቸውን ምህረት የሚጠይቁና እሱም ይቅር የሚላቸው የሆኑ ህዝቦችን ይፈጥር ነበር” (ሙስሊም 2749)፡፡
አላሁ አክበር!! ይህ ውብ ሐዲሥ ጌታ አላህ ምን ያህል ምህረት ማድረግን ወዳድ የሆነ አምላክ መሆኑን ያሳያል፡፡ ኃጢአትን የሚወድ አምላክ ቢሆን ኖሮ፡ ሐዲሡ ‹‹አላህ ያጠፋችሁና፡ ኃጢአትን የሚሰሩ የሆኑ ህዝቦችን ይፈጥር ነበር›› ብሎ ይብቃቃ ነበር፡፡ ጉዳዩ ግን ከምህረት እና ከይቅር ባይነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ‹‹ከዛም ጌታቸውን ምህረት የሚጠይቁና እሱም ይቅር የሚላቸው ›› በማለት ተገለጸ፡፡ ስለዚህ አላህ ተመላሾችን እንጂ በኃጢአት ዘውታሪዎችን አይወዳቸውም፡፡ አምላክ ኃጢአትን ይጠላል እንጂ፡ ኃጢአተኛን ግን ይወዳል ብሎ መስበክ፡ ኃጢአተኞች በድርጊታቸው እንዲጽናኑበት ከመገፋፋት ውጭ ለንሰሀ የሚያነሳሳ ነገር የለውም፡፡ ኃጢአተኛ ወደ አላህ የሚመለሰው የአላህን ምህረትና የሱን ውዴታ ፈልጎ እንዲሁም ቅጣቱንና ኃያልነቱን ፈርቶ ነውና፡ ያለ ተውበትም (ንሰሀ ባይገባም) አላህ እንደሚወደው ከተነገረው ለምን ንሰሀ መግባት አስፈለገው?
ይህ ሀሳብ ማሰቢያው ላልተዛባበት ሰው ግልጽ የሆነ ነገር ነው፡፡ አንዳንዶች ቀኝና ግራውን ቀድመው ሳይመለከቱ፡ ከኋላ ምን ይከተለናል የሚለውን ሳያስከትሉ፡ እንዲሁ በስሜት አምላክ ፍቅሩ ልዩ ነው ለማለት ብቻ ባእድ አስተሳሰብን ያመጡና፡ ከዛም ተመልሰው የማይወጡት ጉድጓድ ስር ይወሸቃሉ፡፡ ዘልሎ ጥልቅ መውጫው ጭንቅ!!
አላህ በደለኞችን አይወድም!! እጃቸውን ከበደላቸው አንስተው በተውበት ካልተመለሱ በስተቀር
አላህ ከሀዲያንን አይወድም!! ወደ እምነት ካልተመለሱ በስተቀር!!
ይህ ነው እውነቱ!!
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


