ኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
” فَإِنْ كُنْتَ فِي شَكٍّ مِمَّا أَنْزَلْنَا إِلَيْكَ فَاسْأَلِ الَّذِينَ يَقْرَءُونَ الْكِتَابَ مِنْ قَبْلِكَ لَقَدْ جَاءَكَ الْحَقُّ مِنْ رَبِّكَ فَلَا تَكُونَنَّ مِنَ الْمُمْتَرِينَ ” سورة يونس 94
“ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ፡፡ እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል፡፡ ከተጠራጣሪዎቹም አትሁን፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 10፡94)፡፡
የዚህን አንቀጽ መልእክት በአግባቡ ለመረዳት ወገኖቻችን አልታደሉም፡፡ በተሳሳተ መንገድ ተረድተው መልክቱን ለነሱ ሊያደርጓትም ቋመጡ፡፡ በድፍረትም እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፡- በዚህ አንቀጽ መሠረት ቅዱስ ቁርኣን ለሙስሊሞች፡ በእምነታቸው ጥርጥር ከገባባቸው መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ዘንድ ሄደው በመጠየቅ እውነቱን መረዳት እንደሚችሉ መጠቆሙን እንረዳለን!!፡፡
ውይ ስታሳዝኑ…. እኔ የምለው፡- እንደው ትክክለኛ ትርጉሙንና መልእክቱን ከማየታችን በፊት፡ እናንተ እንዳላችሁት የ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ›› አንባቢዎችን እንድንጠይቅ ከሆነ ቁርኣኑ የሚገፋፋን፡ ለምን ከናንተ በፊት የነበሩትን አይሁዶቹን አንጠይቅም? ለምን ወደናንተ መምጣት አስፈለገ? ወይስ ቅድሚያ ወደናንተ እንድንመጣ ፈልጋችሁ ነውን?
ደግሞስ እናንተን ነው ቢባል እንኳ ማንን ነው የምንጠይቀው? ካቶሊክን?፣ ኦርቶዶክስን?፣ ፕሮቴስታንትን?፣ ኢየሱስ ብቻ (only jesus) የሚሉትን?፣ የይሆዋ ምስክሮችን (Jihovah witness)?…..? እኮ ማንን? እንጠይቃችሁ ዘንድ ንገሩና! በስም ከፋፍለን የጠራናችሁ፡ በመሐከላችሁ የእምነት ልዩነት መኖሩ የታወቀ ስለሆነ ነው፡፡ ደግሞስ በየትኛው ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ›› መሰረት ላይ ሆናችሁ ነው የምትጠየቁት? 66ቱቨ ወይስ 73ቱ? ወይንስ 81ዱ? ደግሞስ የየትኛው ዓመት እትም? ምረጡልና!!
ወደ ሐቁ ስንመጣ ግን የቅዱስ ቁርኣኑ መልእክት በፍጹም ይህን አያረጋግጥም፡፡ እነሱ የተረዱትን ሀሳብ የሚገልጽ ነገር በቅርቡም ሆነ በሩቁ በቃሉ ውስጥ አይገኝም፡፡ እንዴት? የሚሉ ከሆነና፡ ቀጥተኛ ትርጉሙን መረዳት የሚሹ ከሆነ ማብራሪያውን ከልብ ይከታተሉ፡፡ እውነቱንም ለመረዳት አላህ ያግዘን፡፡ ልባችንንም ያስፋልን፡፡
1ኛ. ጥቅላዊ ማብራሪያ፡-
የአንቀጹ መልእክት፡- የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይነትና ወደሳቸው የሚወርድላቸው መለኮታዊ ራእይ (ቅዱስ ቁርኣን) ከአላህ ዘንድ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የሌለበት መሆኑን እና፡ በዚህ ጉዳይም ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንደማይጠራጠሩና፡ ‹‹ቢጠራጠሩ እንኳ›› ከሳቸው በፊት የነበሩትን የቀደምት መለኮታዊ መጽሐፍት ሊቃውንቶችን በመጠየቅ እውነተኝነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚችሉ ነው፡፡ ምክንያቱም፡- የሳቸው ነቢይነትም ሆነ፡ የቅዱስ ቁርኣን አምላካዊ ቃልነት በመጽሐፎቹ ኦርጂናል ቅጂ ላይ እንደተጠቀሰ ሊቃውንቶቹ ያውቃሉና!!፡፡ ስለዚህም ‹‹እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በርግጥ መጥቶልሀል፡፡ በመሆኑም ከተጠራጣሪዎች አትሁን!›› በማለት፡ እቅጩን በመንገር ጉዳዩን ይደመድመዋል፡፡ አለቀ ደቀቀ፡፡ እውነቱ ያለው እዚሁ ነው፡፡ እዛ እውነት አለና ሂደህ ጠይቅ! የሚል ቃልም ሆነ ፊደል ማግኘት አይቻልም፡፡ ሊቃውንቶቹን ጠይቅ! የተባለው፡ እነሱን እንኳ ብትጠይቃቸው አንተን በሚገባ ያውቁሀል፡፡ ነቢይነትህንም ሆነ የሚወርድልህ ራእይ ከአላህ ዘንድ መሆኑን ይመሰክራሉ ነው፡፡ ይኸው የጌታ አላህ ምስክርነት፡-
“እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ወንዶች ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል፡፡ ከነሱም የተለዩ ክፍሎች እነርሱ የሚያወቁ ሲኾኑ እውነቱን በእርግጥ ይደብቃሉ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡146)፡፡
“እነዚያ መጽሐፍን የሰጠናቸው ልጆቻቸውን እንደሚያውቁ (ሙሐመድን) ያውቁታል፡፡ እነዚያ ከእነርሱ ውስጥ ነፍሶቻቸውን ያከሰሩት እነርሱ አያምኑም፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡20)፡፡
ይህ ነው እውነታው! ከዛ ውጪማ እውነቱን ለማወቅ ከፈለግህ፡ እነሱን ሄደህ ጠይቅ ለማለት ከሆነ፡ በዚያው አንቀጽ ውስጥ ‹‹እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል›› በማለት አስረግጦ መናገር ለምን አስፈለገው? የቃሉ መልእክት ግን፡- እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ብትጠይቃቸው የአንተን ነቢይነትም ሆነ የሚወርድልህን ራእይ (ቅዱስ ቁርኣን) ከአላህ ዘንድ የመጣ መሆኑን ይናገራሉ ነው፡፡ ደግሞም ሊቃውንቶቹ ለሐቅ ያደሩ፡ እውነቱ ሲነገራቸው አምነው የተቀበሉ፡ እንደ ዐብዱላህ ኢብኑ ሰላም (ረዲየላሁ ዐንሁ)፣ እንደ ዐብዱላህ ኢብኑ-ዐምር ኢብኑል-ዓስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) አይነቶቹን እንጂ፡ ለምድራዊ ጥቅማቸው ሲሉ እውነቱን በሀሰት የለወጡ፡ የመጽሐፉን ትክክለኛ መልእክት የደበቁና፡ በመጽሐፉ ላይ እጃቸውን ያስገቡትን አይደለም፡፡ እነዚህን ክፍሎችማ ሄዶ መጠየቅ ለጥመት እንጂ ለምሪት እንደማይጠቅም በሌላ አንቀጽ እንዲህ ይገልጸዋል፡-
“ከመጽሐፉ ባለቤቶች የሆኑ ጭፍሮች ነፍሶቻቸዉን እንጂ የማያሳስቱ ሲሆኑ ሊያሳስቱዋችሁ ተመኙ ግን አያውቁም” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡69)፡፡
2ኛ. ዝርዝር ማብራሪያ፡-
መልእክቱ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንና፡ በአንቀጹ ላይም ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት፡ ወገኖቻችን ካሰቡትና ከቋመጡለት ነገር ጋር ምንም ግኑኝነት እንደሌለው ለማወቅ ይረዳ ዘንድ፡ በኃይለ ቃል እየከፈልን እንመልከተው፡፡
1ኛ. ‹‹ወደ አንተም ካወረድነው›› በሚለው ኃይለ ቃል ውስጥ፡ ከጌታ አላህ ዘንድ ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የወረደ መለኮታዊ ራእይ መኖሩን በቀላሉ እንረዳለን፡፡ ይህም ራእይ ‹‹ቅዱስ ቁርኣን›› ነው፡፡
“እኛ ቁርአንን ባንተ ላይ ማውረድን እኛው አወረድነው።” (ሱረቱ-ደህር (ኢንሳን) 76፡23)፡፡ ከዛም ይቀጥልና፡-
2ኛ. ‹‹በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን›› በማለት ደግሞ አንድን ነገር እንዲያደርጉ ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ ማረጋገጫው ምንድነው? የሚለውን ኋላ ላይ እንመለስበታለን፡፡ ‹‹በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን›› ማለት ግን፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መጠራጠራቸውን የሚያመላክት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቃሉ የሚናገረው ‹‹በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን›› እያለ እንጂ፡ ‹‹በመጠራጠር ውስጥ ነህና›› እያለ አይደለም፡፡
‹ብትሆን› (if) የሚለው ቃል Conditional sentence ነው፡፡ ሊከሰትም ላይከሰትም የሚችል፡ በሁኔታዎች የሚወሰን አያያዥ (conjunction) የሆነ ቃል ነው፡፡
አጠቃላይ ሀሳቡ፡- ወደ ‹‹አንተ ካወረድነው መጽሐፍ (መለኮታዊ ራእይ) ብትጠራጠር እንኳ›› ለማለት ነው፡፡ ታዲያ ምን ይሁን? ከተባለም፡-
3ኛ. ‹‹እነዚያን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ›› በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል፡፡ የመጽሐፉን አንባቢዎች ጠይቅ የሚለው ሀሳብ የሚያያዘው፡ ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን ከሚለው የቁርኣኑ ቃል ጋር እንጂ፡ እውነትን ከፈለግህ ከሚል የፈጠራ ወሬ ጋር አይደለም፡፡ ታዲያ ከየት አምጥታችሁ ነው፡ እውነቱን ከፈለጋችሁ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነቡትን ጠይቁ! ይላል ቁርኣናችሁ የምትሉን?
ከላይ በጥቅላዊ ማብራሪያው ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፡ የመጽሐፍቱን ሊቃውንቶች ብትጠይቃቸው እንኳ፡ በመጽሐፉ ውስጥ በኦርጂናል ይዘቱ የአንተ ነቢይነት እንደተነገረ ያውቃሉ፡ እነሱም ይመሰክራሉ እያለ ነው፡፡
ወገኖቻችን! ‹‹ከአንተ በፊት›› የሚለው ኃይለ ቃል የናንተን ምኞት ከንቱ አያስቀረውምን? ቅዱስ ቁርኣን እየተናገረ ያለው፡- ‹‹ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ›› በማለት እንጂ፡ ከአንተ በኋላ የሚመጡትን ጠይቅ አላለም፡፡ አሁንስ ገባችሁ?
4ኛ. ‹‹እውነቱ ከጌታህ ዘንድ በእርግጥ መጥቶልሃል ከተጠራጣሪዎቹም አትሁን›› በማለት አንቀጹ በሚያምር አገላለጽ ተደመደመ፡፡ አላሁ አክበር! ወደሳቸው ይወርድ የነበረው መለኮታዊ ራእይ፡- እውነቱ እኔው ራሴ ነኝ! ካለ፡ ሌላ እውነት ፍለጋ እንዴት ይኬዳል? ስለዚህ እውነቱ እዚሁ ቁርኣን ውስጥ ነው ያለው፡፡ ‹‹ብትጠራጠር እንኳ እነሱን ጠይቅ›› ማለቱ፡ እውነትን ፍለጋ ወደነሱ ሂድ! ከማለት ጋር ምንም ግኑኝነት የለውም፡፡ ግኑኝነቱ፡ እነሱም ቢሆኑ ብትጠይቃቸው የአንተን ነቢይነት በሚገባ ስለሚያውቁ ይነግሩሀል ነው፡፡
5ኛ. የአላህ ነቢይም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ይህ አንቀጽ በወረደላቸው ግዜ፡ የመጽሐፉን ሰዎች ሄደው አልጠየቁም፡፡ ባይሆን በተቃራኒው እንዲህ ነበር ያሉት፡-
‹‹ላ አሹክኩ ወላ አስአል›› ‹አልጠራጠርም አልጠይቅምም›፡፡ (ተፍሲሩ-ጠበሪይ፡ ጃሚዑል በያን ሱረቱ ዩኑስ 94 ቁጥር 17893-17894)፡፡
እኛም የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ተከታይ የሆንን ሙስሊሞች፡ እሳቸውን በመከተል አንጠይቅምም ደግሞም አንጠራጠርምም፡፡
6ኛ. ኢማሙል ቡኻሪይ በዘገቡት ሶሒሕ ሐዲሥ ላይ ደግሞ፡ እንዲህ የሚል ግሳፄ ተቀምጧል፡-
عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ عَبَّاسٍ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُمَا، قَالَ: ” يَا مَعْشَرَ المُسْلِمِينَ، كَيْفَ تَسْأَلُونَ أَهْلَ الكِتَابِ، وَكِتَابُكُمُ الَّذِي أُنْزِلَ عَلَى نَبِيِّهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ أَحْدَثُ الأَخْبَارِ بِاللَّهِ، تَقْرَءُونَهُ لَمْ يُشَبْ، وَقَدْ حَدَّثَكُمُ اللَّهُ أَنَّ أَهْلَ الكِتَابِ بَدَّلُوا مَا كَتَبَ اللَّهُ وَغَيَّرُوا بِأَيْدِيهِمُ الكِتَابَ، فَقَالُوا: هُوَ مِنْ عِنْدِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا، أَفَلاَ يَنْهَاكُمْ مَا جَاءَكُمْ مِنَ العِلْمِ عَنْ مُسَاءَلَتِهِمْ، وَلاَ وَاللَّهِ مَا رَأَيْنَا مِنْهُمْ رَجُلًا قَطُّ يَسْأَلُكُمْ عَنِ الَّذِي أُنْزِلَ عَلَيْكُمْ ” رواه البخاري 2685.7522.7523
ዐብዱላህ ኢብኑ-ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡- “እናንተ ሙስሊሞች ሆይ! በነቢዩ ላይ የተወረደላችሁ መጽሐፍ (ቁርኣን) ከአላህ ዘንድ የመጣ አዲስ (ያላረጀ) ሆኖ ሳለ፡ እናንተም ያልተበረዘና የሰው እጅ ያልገባበት ሆኖ እያነበባችሁት፡ የመጽሐፉን ሰዎች (አይሁዶችና ክርስቲያኖች) እንዴት ትጠይቃላችሁ? አላህም (በቁርኣኑ) የመጽሐፉ ሰዎች መጽሐፉን በእጃቸው እንደበረዙትና እንደቀየሩት፣ ከዛም የተበረዘውን ጥቂትን ምድራዊ ዋጋ ለመሸመት፡ ይህ ከአላህ ዘንድ የመጣ ነው እንዳሉ ነግሯቹኋል፡፡ እንግዲያውስ ወደናንተ የመጣላችሁ ዕውቀት እነሱን ከመጠየቅ አይከለክላችሁምን? በአላህ ይሁንብኝ! ከነሱ ውስጥ አንድም ሰው ወደናንተ ስለወረደው ሲጠይቁአችሁ በፍጹም አላየንም (ታዲያ እናንተ እነሱን እንዴት ትጠይቃላችሁ?)” (ቡኻሪይ 2685፣ 7522፣ 7523)፡፡
አዎ! ልንጠይቃቸውም አይገባም! ትክክለኛው ሀሳብ ይህ ነው ወላሁ አዕለም፡፡
“ጌታህ በመካከላቸው በትክክል ፍርዱ ይፈርዳል፤ እርሱም አሸናፊው ዐዋቂው ነው። በአላህም ላይ ተጠጋ፤ አንተ ግልጽ በሆነው እውነት ላይ ነህና።” (ሱረቱ-ነምል 27፡79)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


