ኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ሥም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በኾነው
“ከአልረሕማን (ቅጣት) በሌሊትና በቀን የሚጠብቃችሁ ማነው» በላቸው፡፡ በእውነቱ እነሱ ከጌታቸው ግሳጼ (ከቁርአን) ዘንጊዎች ናቸው፡፡” (ሱረቱል አንቢያእ 21፡42)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ቅጣት የሚለው ቃል በቅንፍ ታጥሯል፡፡ በቅንፍ መታጠሩን የተመለከቱ አንዳንድ ወገኖች፡ ይህ በዐረብኛው ቁርኣን ላይ የሌለ፡ በአማርኛው ቁርኣን ላይ የገባ አዲስ ተጨማሪ ሀሳብ ነው የሚል አስቂኝ እና አሳዛኝ ተቃውሞ ያሰማሉ፡፡ የቅንፉን አስፈላጊነት፡ የቃሉንም መልእክት በተወሰነ መልኩ ማብራራት ግን የኛ ግዴታ ነው፡፡
ይህን የምናደርገው፡- በዚህ ሰበብ ትምሕርት የሚያገኙ ወንድምና እህቶች ስለሚኖሩ፡ ከወገኖችም በኩል ጥላቻ ልቡን ያላጠቆረው ካለ እውነታውን እንዲረዳ ለማገዝና፡ ከተቻለም በአላህ ፈቃድ ሰበቡል-ሂዳያ ለመሆን ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ዝምታና ንቀት ለነሱ በቂ መልስ የሚሆንበት ሁኔታ አልለ። ግን የሚያነበው ሰው በዛ ካለ: ባጋጣሚ የተገኘውን ሰው በሰበቡ ማስተማሩ በላጭ ኾኖ ስለሚገኝ። ከጥሩ የተሻለ ጥሩ መምረጥ ደግሞ የሙስሊሞች ጥበብ ነው። ወማ-ተውፊቂ ኢልላ ቢላህ!! መልካም ንባብ፡-
1ኛ/ አንድ ሙስሊም ያልሆነ ሰው ከእናንተ ጋር ስለ እምነት ጉዳዮች እየተወያየ፡ በቁርኣን ትርጉሞች ላይ የተቀመጡትን በቅንፍ የታጠሩ ቃላት በማንሳት፡- ይህ በዐረብኛው ቁርኣን ላይ የሌለ፡ በተርጓሚዎች የተጨመረ ሀሳብ ነው ካላችሁ፡ የናንተም ቀዳማይ ጥያቄ መሆን ያለበት፡- ዐረብኛው ላይ ያለውን ቃል ታውቀዋለህን? የሚል ነው፡፡ አላውቀውም ካለ፡ እንዴት የማታውቀውን ነገር ምን ምን እንዳለውና ምን ምን እንደሌለው ለመናገር ደፈርክ ታዲያ? ይባላል፡፡ አውቀዋለሁ ካለ ደግሞ፡ እስኪ የዐረብኛውን ንባብ በአማርኛ ጻፈው በማለት ልንፈትነው ይገባል፡፡ በአንድ ትርጉም ውስጥ ያለው ቃል በዋናው ውስጥ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ የሚችለው ሁለቱንም ቋንቋ ማንበብና ማመሣከር የሚችል ሰው ብቻ ነውና።
ምክንያቱም ሰው ካላወቀ አስረዱኝ በማለት በትህትና ይጠይቃል፡ ካወቀ ደግሞ በዕውቀቱ ልክ ይወያያል እንጂ፡ በድፍረት የማያውቀውን እንደሚያውቅ ሆኖ አይቀርብም፡፡ ለንደዚህ አይነቱ ደግሞ የሚጠቅመው የዋህነት ሳይኾን፡ በማፋጠጥ አለማወቁን መንገር ነው፡፡
2ኛ/ ቁርኣን ቃሉንና መልእክቱን ወደ አማርኛ የተረጎሙት ሊቃውንቶች አንዳንድ ቃላትን በቅንፍ ያጠሩት፡ ከቁርኣኑ ውጭ የኾነ የግል ትርጓሜ ስለኾነ አይደለም፡፡ እነሱም ቅንፍን የተጠቀሙት ለምን ዓላማ እንደኾነ በአማርኛው ቅዱስ ቁርኣን ትርጉም መቅድም ላይ እንዲህ ተናግረዋል፡-
‹‹በዐረብኛው አነጋገር ውስጠ ታዋቂ ኾኖ ሳለ በአማርኛው መግለጽ በሚያስፈልገው ላይ የቁርኣን አታቾች በሰጡት ፍቺ መሠረት ገልጸን በቅንፍ አጥረነዋል›› 3ኛው ሀሳብ ላይ።
ይህ ነው የቅንፍ ዋና መልእክት፡፡ ሀሳቡ በዐረብኛው ላይ ያለ ውስጠ-ታዋቂ ሆኖ፡ ዐረብኛን ለሚችል ሰው ግልጽ የኾነ፡ ወደሌላ ቋንቋ በሚተረጎምበት ጊዜ ግን: ያ ውስጠ ታዋቂ ሀሳብ በቅንፍ ተገልጾ መቀመጥ እንዳለበት የመስኩ ምሁራን ስለመከሩ በዚህ መልክ በቅንፍ ተገልጾ ተቀምጧል ነው፡፡ ሁሉም ቋንቋ የራሱ የኾነ ሰዋሰዋዊ አወቃቀር አለውና። ከዛ በተረፈ፡ በቁርኣኑ ላይ የሌለ፡ አዲስ ሀሳብ ልክ እንደ ሌሎች የሃይማኖት መጽሐፍት በትርጉም ላይ እጃቸውን አስገብተው አልተጫወቱበትም፡፡
3ኛ/ ከላይ እንደ-ምሣሌ ወደቀረበው አንቀጽ ማብራሪያ ስንመለስ፡ የአንቀጹ መልእክት ሰዎች ከአል-ረሕማን ቅጣት፡ በቀንም ኾነ በለሊቱ ክፍል ማንም ሊከላከልላቸው እንደማይችል እየገለጸ ነው፡፡ እሱ አላህ በኃጢአታቸው ሰበብ ሊቀጣቸው ከፈለገ፡ ከሱ ቅጣት ማንም ሊያድናቸው የሚችል የለም እያለ ነው፡፡ በዚህ ትርጉም ውስጥ በቅንፍ የገባው ቅጣት የሚለው ቃል የተጨመረ አዲስ ሀሳብ ሳይኾን፡ በዋናው ዐረብኛ ውስጥም በውስጠ ታዋቂነት ያለ መኾኑን በሦስት መንገድ ማብራራት ይቻላል፡፡ እነሱም፡-
ሀ/ ቃሉ ከበፊቱ ካለ አንድ አንቀጽ ጋር ይገናኛል፡፡ ይህን አንቀጽ ስንመለከተው የሚናገረው ስለ ቅጣት መኾኑ የበለጠ ግልጽ ይኾንልናል፡፡ የበፊቱ አንቀጽ እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹ከአንተ በፊትም የነበሩት መልክተኞች በእርግጥ ተቀለደባቸው፡፡ በእነዚያም ከእነሱ ይቀልዱ በነበሩት በርሱ ይሳለቁበት የነበሩት (ቅጣት) ሰፈረባቸው፡፡›› (ሱረቱል አንቢያእ 21፡41)፡፡
ጌታ አላህ በዚህ አንቀጽ ሥር፡ ቀደምት ነቢያት ላይ ሲያሾፉና ሲሳለቁ የነበሩትን ሕዝቦች አላህ በቅጣት እንዳጠፋቸው፡ ለነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እየገለጸላቸው ነው፡፡ ከዛ በመቀጠል፡ አሁን ያሉት ደግሞ፡ የሳቸውን ነቢይነት ባይቀበሉና ቢያስተባብሉ፡ ጌታ አላህ እነዚህንም ልክ እንደ-ቀደምቶቹ፡ እንደሚቀጣቸውና፡ ከሱ ቅጣትም ማንም ሊታደጋቸው እንደማይችል እየነገራቸው፡ ከጌታቸው ቅጣት በፊት ወደ እምነት እንዲመለሱ ሲያስታውሳቸው፡- ‹”ከአልረሕማን (ቅጣት) በሌሊትና በቀን የሚጠብቃችሁ ማነው?» በላቸው በማለት ተናገረ፡፡
ለ/ በሌላ የቅዱስ ቁርኣን ክፍል ላይ ሰዎች በተኙበት በሌሊት፡ ወይም ለሥራ በተሰማሩበት በጠዋቱ (ረፋድ ላይ) ክፍለ-ጊዜ አላህ ቅጣቱን ቢልክባቸው፡ ማንም እንደማያድናቸው በመግለጽ፡ ካሉበት የዝንጋቴ ሕይወት በመላቀቅ፡ ወደ ጌታቸው መንገድ እንዲመጡ ይናገራል፡፡ ቃሉ እንዲህ ይነበባል፡-
“የከተማዋ ሰዎችም እነሱ የተኙ ኾነው ቅጣታችን ሌሊት ሊመጣባቸው አይፈሩምን? የከተማዋ ሰዎችም እነሱ የሚጫወቱ ኾነው ሳሉ ቅጣታችን ቀን በረፋድ ሊመጣባቸው አይፈሩምን” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡97-98)፡፡
የመጀመሪያውም አንቀጽ የሚናገረው፡- በቀንም ሆነ በለሊት ከአል-ረሕማን ቅጣት ማንም ሊያድነን የሚችል እንደሌለ ነው፡፡
ሐ/ አንድ አባት ልጁን:– ልጄ ሆይ! ከኔ ማን ያስጥልሀል? ብሎ ቢጠይቀው: ልጁም የሚረዳው: አባቱ እሱን ሊቀጣው ከፈለገ ማንም እንደማያስጥለው ነው። ስለሆነም ቶሎ በመሸሽ ወደእናቱ ጉያ: እሱ አያዋጣኝም ካለም ወደ አባቱ በመመለስ ይቅርታውን ይጠይቃል። እናንተም ወገኖች ሆይ! ከአላህ ቅጣት የሚያተርፋችሁ ማንም ስለሌለ: በፍጥነት ወደ አላህ ሽሹ ቃሉም እንዲህ ይላል:–
“ወደ አላህም ሽሹ፤ እኔ ለናንተ ርሱ ግልጽ አስጠንቃቂ ነኝና (በላቸው)” (ሱረቱ–ዛሪያት 51:50)።
አላህ የህዲኩም፣ ወዩሠቢትና
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


