ኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ሥም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
” فَأَزَلَّهُمَا الشَّيْطَانُ عَنْهَا فَأَخْرَجَهُمَا مِمَّا كَانَا فِيهِ وَقُلْنَا اهْبِطُوا بَعْضُكُمْ لِبَعْضٍ عَدُوٌّ وَلَكُمْ فِي الْأَرْضِ مُسْتَقَرٌّ وَمَتَاعٌ إِلَى حِينٍ ” سورة البقرة 36
“ከርሷም ሰይጣን አዳለጣቸው በውስጡም ከነበሩበት (ድሎት) አወጣቸው፡፡ «ከፊላችሁም ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ፤ ለናንተም በምድር ላይ እስከ ጊዜ (ሞታችሁ) ድረስ መርጊያና መጣቀሚያ አላችሁ» አልናቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡36)፡፡
” قَالَ اهْبِطُوا بَعْضُكُمْ لِبَعْضٍ عَدُوٌّ وَلَكُمْ فِي الْأَرْضِ مُسْتَقَرٌّ وَمَتَاعٌ إِلَى حِينٍ ” سورة الأعراف 24
“(አላህ) « ከፊላችሁ ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ፡፡ ለእናንተም በምድር ላይ እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ መርጊያና መጠቀሚያ አላችሁ» አላቸው፡፡” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡24)፡፡
በነዚህ ሁለት ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾች መሠረት ‹‹ከፊላችሁ ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ!›› የሚል ቃል አልለ፡፡ ይህ ጠላትነት በማን እና በማን መሐል ያልለ ነው? የሚል ጥያቄ ከአንድ ወንድሜ በኩል ስለቀረበልኝ፡ መጠነኛ ማብራሪያ ለመስጠት ነው ኢንሻአላህ፡፡
1ኛ/ በሰውና በኢብሊስ ዝርያዎች መሐል፡- ይህ አንደኛው ትርጉም ነው፡፡ በአደምና በኢብሊስ መሐል ጠላትነት እንደሰፈነው ኹሉ፡ በዛው መልኩ በአደም ዝርያዎችና በኢብሊስ ዝርያዎች መሐል ጠላትነት ሰፍኗል፡፡ ቂያማህ እስኪቆም ድረስ ከፊሉ ለከፊሉ ጠላት ኾኖ ይቀጥላል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“ሰይጣን ለናንተ ጠላት ነው፡፡ ስለዚህ ጠላት አድርጋችሁ ያዙት፡፡ ተከታዮቹን የሚጠራው ከእሳት ጓዶች እንዲኾኑ ብቻ ነው፡፡” (ሱረቱ ፋጢር 35፡6)፡፡
“እናንተ ሰዎች ሆይ! በምድር ካለው ነገር የተፈቀደ ጣፋጭ ሲኾን ብሉ፡፡ የሰይጣንንም እርምጃዎች አትከታተሉ፡፡ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡168)፡፡
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ሁላችሁም በመታዘዝ ውስጥ ግቡ፡፡ የሰይጣንንም እርምጃዎች አትከተሉ፤ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡208)፡፡
“ከለማዳ እንስሳዎችም የሚጫኑትንና የማይጫኑትን (ፈጠረ)፡፡ አላህ ከሰጣችሁ ሲሳይ ብሉ፡፡ የሰይጣንንም እርምጃዎች አትከተሉ፡፡ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡142)፡፡
“ሰይጣንም አያግዳችሁ፡፡ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና፡፡” (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 43፡62)፡፡
በነዚህ አንቀጾች መሠረት፡ ሸይጧን ለኛ ለሰዎች ግልጽ ጠላታችን በመኾኑ ምክንያት፡ እኛም ጠላት አድርገን ልንይዘው ይገባል፡፡ ሁለቱን ወላጆቻችንን አደም እና ሐዋእን (ዐለይሂማ-ሰላም) ከጀነት እንዲወጡ ሰበብ እንደኾናቸው ኹሉ፡ እኛንም እንዳይፈትነን መጠንቀቅ እንዳለብን ጌታ አላህ እንዲህ ይመክረናል፡-
“የአደም ልጆች ሆይ! ሰይጣን አባትና እናታችሁን ኀፍረተ ገላቸውን ሊያሳያቸው ልብሶቻቸውን ከነሱ የገፈፋቸው ሲኾን ከገነት እንዳወጣቸው ሁሉ እናንተን አይሞክራችሁ፡፡ እነሆ እርሱ ከነሰራዊቱ ከማታዩዋቸው ስፍራ ያዩዋችኋልና፡፡ እኛ ሰይጣናትን ለእነዚያ ለማያምኑት ወዳጆች አድርገናል፡፡” (ሱረቱል እዕራፍ 7፡27)፡፡
2/ በሰው ዘር መካከል፡- ይህ ደግሞ ሌላኛው ትርጉም ነው፡፡ ሁለቱም ክፍሎች የአባታችን የአደም (ዐለይሂ-ሰላም) ዝርያ ኹነው፡ በመካከላቸው ከፊሉ ለከፊሉ ጠላት የኾነ ማለት ነው፡፡ ይህም በሁለት መንገድ ነው፡፡
አንደኛው፡- በእምነት ጉዳይ የኾነ ማለት ነው፡፡ ማለትም የነቢያትን እምነት በቃልም ኾነ በተግባር የሚከተሉ አማኞች (ሙስሊሞች) ነቢያትን ከማይከተሉ ከሀዲያን (ኩፋር) ጋር ሁሌም ጠላት ናቸው፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር ምንም አይነት ልባዊ ወዳጅነት መመስረት አይችሉም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም አማኞች የአላህ ወዳጅ ናቸው፡፡ ከሀዲያን ደግሞ የሸይጧን ወዳጅ ናቸው፡፡ የአላህ ወዳጅ የኾኑ አማኞች፡ የአላህ ጠላት እና የሸይጧን ወዳጅ ከሆኑ ከሀዲያን ጋር ወዳጅነትን እንዳይመሰርቱ እምነታቸው ይከለክላቸዋልና፡፡ እምነትንና አማኞችን የወደደ፡ ክህደትንና ከሀዲያንን እንዳይወድ እምነቱ ሊከለክለው ግድ ነው፡፡ የአላህ ቃል ስለ አባታችን ኢብራሂም (ዐለይሂ-ሰላም) እንዲህ ይነግረናል፡-
“በኢብራሂምና በእነዚያ ከእርሱ ጋር በነበሩት (ምእምናን) መልካም መከተል አለቻችሁ፡፡ ለሕዝቦቻቸው «እኛ ከእናንተ ከአላህ ሌላ ከምትግገዙትም ንጹሖች ነን፡፡ በእናንተ ካድን፡፡ በአላህ አንድ ብቻ ሲኾን እስከምታምኑ ድረስ በእኛና በእናንተ መካከል ጠብና ጥላቻ ዘወትር ተገለጸ፡፡» ባሉ ጊዜ (መልካም መከተል አለቻችሁ)…” (ሱረቱል ሙምተሒናህ 60፡4)፡፡
“በምድርም ላይ በተጓዛችሁ ጊዜ እነዚያ የካዱት ያውኩናል ብላችሁ ብትፈሩ ከሶላት (ባለ አራት ረከዓት የኾኑትን) ብታሳጥሩ በናንተ ላይ ኀጢአት የለም፡፡ ከሓዲዎች ለእናንተ በእርግጥ ግልጽ ጠላቶች ናቸውና፡፡” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡101)፡፡
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ጠላቶቼንና ጠላቶቻችሁን ወዳጆች አድርገችሁ አትያዙ፡፡ ከእውነቱ የመጣላችሁን ሃይማኖት በእርግጥ የካዱ ሲኾኑ ውዴታን ወደእነርሱ ታደርሳላችሁ፡፡ መልክተኛውንና እናንተን በአላህ በጌታችሁ ስላመናችሁ (ከመካ) ያወጣሉ፡፡ በመንገዴ ለመታገልና ውዴታዬን ለመፈለግ የወጣችሁ እንደኾናችሁ (ወዳጆች አድርጋችሁ አትያዙዋቸው)፡፡ እኔ የምትደብቁትንና የምትገልጹትን ሁሉ የማውቅ ስኾን ወደእነርሱ በፍቅር ትመሳጠራላችሁ፡፡ ከእናንተም (ይህንን) የሚሠራ ሰው ቀጥተኛውን መንገድ በእርግጥ ተሳሳተ፡፡ ቢያሸንፏችሁ ለእናንተ ጠላቶች ይኾናሉ፡፡ እጆቻቸውንና ምላሶቻቸውንም ወደእናንተ በክፉ ይዘረጋሉ፡፡ ብትክዱም ተመኙ፡፡ ዘመዶቻችሁም፣ ልጆቻችሁም በትንሣኤ ቀን አይጠቅሟችሁም፤ (አላህ) በመካከላችሁ ይለያል፡፡ አላህም የምትሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው፡፡” (ሱረቱል ሙምተሒናህ 60፡1-3)፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፡- ከእምነትም ባሻገር፡ በምድራዊ ጸጋዎች በመፎካከርና በስግብግብነት አንዱ ለሌላው ጠላት ኾኖ መነሳቱን የሚጠቁም ነው ማለት ነው፡፡ በጥቅሉ ‹‹ከፊላችሁ ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ!›› የተባለው የሚያመላክተን፡ በሰውና በኢብሊስ ዝርያዎች መሐል ያለውን ዘላለማዊ ጠላትነትና፡ እንዲሁም በሰው ዘር መሐል በአማኞችና በከሀዲያን መሐል ያለውን ጠላትነት ነው፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡ አላህ እውነታውን ዐዋቂ ነው፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


