ኡስታዘአቡ ሀይደር
በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ውዳሴና ሰላም የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለኾኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ታሀ 47)፡፡
1ኛ/ ቅዱስ ቁርኣን የአላህ ቃል ነው፡፡ ቃሉም ሆነ መልእክቱ የአላህ ብቻ ነው፡፡ በቁርኣን ውስጥ የመላእክት፣ የነቢያት፣ የጸሐፊዎች፣ የአጋንንት ቃልና ሀሳብ አልሰፈረም አይሰፍርምም፡፡ በቁርኣን ውስጥ ተናጋሪው ጌታ አላህ ብቻ ነው፡፡ ስለ ነቢያት የሚተርክልን፣ ስለ መላእክት የሚያወሳልን፣ ይህን አድርጉ ያንን ደግሞ አትቅረቡ! በማለት የሚያናግረን እሱ ጌታ አላህ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሙስሊም ቁርኣንን ከፍቶ አነበበ ማለት፡ ጌታ አላህን አናገረው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በውስጡ የሰፈረው ቃል በጠቅላላ ተናጋሪው አላህ በመኾኑ ማለት ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” وَإِنْ أَحَدٌ مِنَ الْمُشْرِكِينَ اسْتَجَارَكَ فَأَجِرْهُ حَتَّى يَسْمَعَ كَلَامَ اللَّهِ ثُمَّ أَبْلِغْهُ مَأْمَنَهُ ذَلِكَ بِأَنَّهُمْ قَوْمٌ لَا يَعْلَمُونَ ” سورة التوبة 6
“ከአጋሪዎችም አንዱ ጥገኝነትን ቢጠይቅ #የአላህን_ቃል ይሰማ ዘንድ አስጠጋው፡፡ ከዚያም ወደ መጠበቂያው ስፍራ አድርሰው፡፡ ይህ እነሱ የማያውቁ ሕዝቦች በመኾናቸው ነው፡፡” (ሱረቱ-ተውባህ 9፡6)፡፡
2ኛ/ ቅዱስ ቁርኣን ከጌታ አላህ ዘንድ ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ አለይሂ ወሰለም) ልብ የወረደው በመልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) በኩል ነው፡፡ እንደሚታወቀው ወሕይ (መለኮታዊ ራእይ) ከጌታ አላህ ወደ ነቢያት ሲተላለፍ፡ በሶስት መንገዶች ነው (ሱረቱ-ሹራ 42፡51)፡፡ የመጀመሪያው፡- በራእይ ወይም በህልም አማካኝነት ለነቢይነት ወደተመረጠው ግለሰብ ይወርዳል፡፡ ልክ ነቢ ኢብራሂም (ዐለይሂ-ሰላም) ልጁን ኢስማዒልን እንዲያርድ ከአላህ በኩል በህልሙ ትእዛዝ እንደመጣለት ማለት ነው (ሱረቱ-ሷፍፋት 37፡101-112)፡፡
በሌላኛው መንገድ ደግሞ፡- ቀጥታ የአላህ ቃል ያለ መልአክ ጣልቃ-ገብነት ወደ ተመረጠው ነቢይ በመድረስ፡ ያ ነቢይ የአላህን ቃል በጆሮው እያዳመጠ ትእዛዛትን ይቀበላል፡፡ ልክ ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) በሲናእ ተራራ ላይ ለዐርባ ቀናት ያህል የጌታውን ቃል እንደሰማውና፡ ጌታው አላህም እሱን እንዳናገረው ማለት ነው (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡164፣ ሱረቱል አዕራፍ 7፡143)፡፡
በሶስተኛው መንገድ ደግሞ፡- በጌታ አላህ እና ለነቢይነት በተመረጠው ግለሰብ መካከል፡ መልአክ ይመረጥና፡ ያ መልአክ (ጂብሪል) ከአላህ ራእይን እየተቀበለ፡ አድርስ ወደተባለው ነቢይ ዘንድ ሄዶ የአላህን ቃል ያለ-ምንም ጭመራና ቅነሳ ያስተላልፋል ማለት ነው (ሱረቱ-ነሕል 16፡2)፡፡ ቅዱስ ቁርኣን ወደ ረሱላችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ልብ የተወረደው፡ በዚህ በሶስተኛው መንገድ በመልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) በኩል ነው፡፡ ቀጣዮች ቁርኣናዊ አንቀጾች ይህንን ሀሳብ ይበልጥ ያብራራሉ፡-
“ለጂብሪል ጠላት የኾነ ሰው (በቁጭት ይሙት) በላቸው፡፡ እርሱ (ቁርኣኑን) ከበፊቱ ለነበሩት (መጻሕፍት) አረጋጋጭ ለምእመናን መሪና ብስራት ሲኾን በአላህ ፈቃድ በልብህ ላይ አውርዶታልና፡፡” (ሱረቱል-በቀራህ 2፡97)፡፡
“እነዚያን ያመኑትን ለማረጋጋት ሙስሊሞቹንም ለመምራትና ለማብሰር (ቁርኣንን) ቅዱሱ መንፈስ (ጂብሪል) እውነተኛ ሲኾን ከጌታህ አወረደው በላቸው፡፡” (ሱረቱ-ነሕል 16፡102)፡፡
“እርሱም (ቁርኣን) በእርግጥ ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡ እርሱን ታማኙ መንፈስ (ጂብሪል) አወረደው፤ ከአስፈራሪዎቹ (ነቢያት) ትኾን ዘንድ በልብህ ላይ (አወረደው)፡፡” (ሱረቱ-ሹዓራእ 26፡192-194)፡፡
3ኛ/ ቅዱስ ቁርኣን ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ልብ የወረደው በዐረብኛ ቋንቋ ነው፡፡ ማንኛውም ነቢይና መልክተኛ ራእይ የሚወርድለት፡ የተላከበት ማኃበረሰብ (ሕዝቦቹ) በሚረዱትና በሚገባቸው ቋንቋ ነው (ሱረቱ-ኢብራሂም 14፡4)፡፡ ነቢያችን (ሶለላሁ አለይሂ ወሰለም) የተላኩት ለመላው የዓለም ሕዝብ ቢሆንም፡ የዳዕዋው ጅማሬ ከገዛ ሀገራቸው ስለሆነ የሚነሳው፡ መለኮታዊው ራእይ በዐረብኛ ቋንቋ ሆነ ማለት ነው፡፡ ከአንድ አካባቢ የተነሳ ወንዝ፡ ሌላ ስፍራ ሄዶ የሚያገለግለው፡ ቅድሚያ አካባቢውን ካዳረሰ በኋላ ነውና፡ የቁርኣንም መልክት ለመላው የሰው ልጆች ይዳረስ ዘንድ፡ በየጊዜው አላህ በሚያስነሳቸው የኢስላም ሊቃውንት ሰበብ፡ የቁርኣን መልእክት በየሀገሩ ቋንቋ እየተተረጎመ ተሰራጨ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ቁርኣን በዐረብኛ ቋንቋ ለመውረዱ ቀጣዮቹ ቁርኣናዊ አንቀጾች እንዲህ ይናገራሉ፡-
“እኛ (ፍቹን) ታውቁ ዘንድ ዐረብኛ ቁርኣን ሲሆን በእርግጥ አወረድነው፡፡” (ሱረቱ ዩሱፍ 12፡2)፡፡
“እንደዚሁም ዐረብኛ ቁርኣን ኾኖ አወረድነው፡፡ አላህንም ይፈሩ ዘንድ ወይም ለእነሱ ግሣጼን ያድስላቸው ዘንድ ከዛቻ ደጋግመን በውስጡ ገለጽን፡፡” (ሱረቱ ጣሀ 20፡113)፡፡
“በዚህም ቁርኣን ውስጥ ለሰዎች ይገሠጹ ዘንድ ከየምሳሌው ሁሉ በእርግጥ አብራራን፡፡ መዛባት የሌለበት ዐረብኛ ቁርኣን ሲኾን (አብራራነው)፡፡ ሊጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡” (ሱረቱ-ዙመር 39፡27-28)፡፡
በተጨማሪም፡- (ሱረቱ-ረዕድ13፡37፣ ሱረቱ ፉሲለት 41፡3፣ ሱረቱ-ሹራ 42፡7፣ ሱረቱ-ዙኽሩፍ 43፡3 ይመልከቱ)፡፡
4ኛ/ ቅዱስ ቁርኣን ከጌታ አላህ ዘንድ ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ልብ ሲወርድ በጠቅላላ አንድ ጊዜ አልወረደም፡፡ 23 ዓመታትን በፈጀ ዘመን ውስጥ፡ እንደ አስፈላጊነቱ በሱራዎችና በአንቀጾች ተከፋፍሎ ነው ቀስ በቀስ የወረደው፡፡ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ስለ አንድ የእምነት ጉዳይ ሲጠይቁ ለዚያ ምላሽ ይኾን ዘንድ፣ወይንም አንድን ነገር ይሠሩትና ይፈጽሙት ዘንድ ህግ መደንገግ ሲያስልግ፣ ወይንም አንድን ነገር ይርቁትና ይጠነቀቁት ዘንድ ገደብ ማበጀት ሲያስፈልግ አንድ ሙሉ የቁርኣን ሱራ፡ ወይንም የተወሰኑ አያቶች (አናቅጽ) በጉዳይ ላይ በመመርኮዝ ይወርዳል ማለት ነው፡፡
ለምሣሌ፡- የአላህን ባሕሪያት እንዲሁም ፍጹማዊ አንድነቱን የሚናገረውን የቁርኣንን ክፍል ሱረቱል ኢኽላስን ብንወስድ፡ ይህ ሱራ የወረደበት ሰበብ፡- በወቅቱ የነበሩ ዐረብ ጣኦታውያን (ሙሽሪኩል ዐረብ) ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ አለይሂ ወሰለም) ዘንድ በመምጣት፡- ይህ እኔን መልክተኛ አድርጎ ልኮኛል በማለት፡ የምታመልከውና የምትሰብከውን ጌታ ምንነት ግለጽልን! ብለው በጠየቁ ጊዜ፡ ሱራው ለጥያቄአቸው ምላሽ ኾኖ ወረደ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ቁል›› የሚል ትእዛዛዊ ግሥን በአንቀጹ መጀመሪያ ላይ ያስቀደመው፡፡
ሌላ ምሣሌ፡- 109ኛውን ሱራ “ሱረቱል ካፊሩንን” እንውሰድ፡፡ ጣኦታውያን የነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሃይማኖታዊ ስብከት በኃይል ማስቆም ሲያቅታቸው፡ ወደሳቸው ዘንድ በመምጣት፡- በቃ አንድ አመት የኛን (የሀሰት) አማልክት ከኛ ጋር አምልክ፣ በቀጣዩ አመት ደግሞ፡ እኛ የአንተን (እውነተኛ) አምላክ እናምልክ! ብለው ሀሳብ አቀረቡ፡፡ በምላሹም፡- እናንተ ከሀዲያን ሆይ! እኔ እናንተ የምትገዟቸውን የሃሰት አማልክት አልገዛም! ብለህ ነገራቸው የሚል “ሱረቱል ካፊሩን” የተሰኘው መለኮታዊ ቃል፡ ሙሉ ሱራው ወረደ ማለት ነው፡፡ (ተፍሲር ሐዳኢቁ-ሩሒ ወር-ረይሓን፡ ሸይኽ ሙሐመዱል-አሚን ኢብኑ ዐብዲላህ አል-ሀረሪይ)፡፡
ቅዱስ ቁርኣን በቀስታ እየተከፋፈለ ለመውረዱ ማሥረጃ ካስፈለገ፡ ቀጣዮቹን አንቀጾች እናስተውላቸው፡-
“ከርሱ በፊት ያሉትን መጻሕፍት የሚያረጋግጥ ሲኾን መጽሐፉን (ቁርኣንን) ባንተ ላይ #ከፋፍሎ በእውነት አወረደ፡፡ ተውራትንና ኢንጂልንም አውርዷል፡፡” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡2)፡፡
“ቁርኣንንም በሰዎች ላይ በዝግታ ላይ ኾነህ ታነበው ዘንድ #ከፋፈልነው፡፡ #ቀስ_በቀስ ማውረድንም አወረድነው፡፡” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡106)፡፡
“እነዚያ የካዱትም «ቁርኣን በእርሱ ላይ ለምን በጠቅላላ አንድ ጊዜ አልተወረደም» አሉ፡፡ እንደዚሁ በእርሱ ልብህን ልናረጋ (ከፋፍለን አወረድነው)፡፡ ቀስ በቀስ #መለያየትንም ለየነው፡፡” (ሱረቱል ፉርቃን 25፡32)፡፡
5ኛ/ ቅዱስ ቁርኣን ከጌታ አላህ ዘንድ ወደ ነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ልብ ሲወርድ፡ በልቦናም ሆነ በጽሑፍ ደረጃ ተጠብቆ እንዲቆይ ጌታ አላህ ቃል ገብቶለታል፡፡ ቁርኣኑን የመጠበቅ ኃላፊነትን ለሳቸው ወይንም ለሶሓቦቹ አልሰጠም፡፡ እሳቸው የወረደላቸውን የአላህ ቃል ለሕዝቦቻቸው በቃልም ሆነ በተግባር በማብራራት እንዲያደርሱ ሲታዘዙ፣ እነሱ ሶሓቦቹ (ረዲየላሁ ዐንሁም) ደግሞ፡ በደረሳቸው የአላህ ቃል መሠረት፡ ቃሉን እንዲያነቡና እንዲሰሩበት ታዝዘዋል፡፡ ቃሉን ለመጠበቅ ኃላፊነቱን ግን አላህ ወስዶታል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡” (ሱረቱል ሒጅር 15፡9)፡፡
መልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) ከአላህ ዘንድ የተሰጠውን የቁርኣን ክፍል ወደሳቸው ዘንድ በመምጣት በሚያነብላቸው ወቅት፡ እሳቸውም ይጠፋብኛል በሚል ስጋት፡ ወዲው ከመልአኩ አንዲትን ቃል እንደሰሙ፡ ወሕዩ ከማለቁ በፊት፡ የሰሙትን ነገር በመደጋጋም ለመሐፈዝ ፡ምላሳቸውን በፍጥነት ያንቀሳቅሱ ነበር፡፡ ጌታ አላህም፡- ይህን ቁርኣን እንዳይጠፋና እንዳትረሳው በማድረግ (የተሻሩ የህግ አንቀጾች ሲቀሩ) ባንተ ልብ ላይ ሰብስቦ ማስቀመጡ የኔ ድርሻ ነውና፡ በቁርኣን ንባብ ላይ አትቸኩል፡፡ የመጣልህ መልእክትም እስኪጠናቀቅ ድረስ አዳምጠው፡፡ ከዛም ባንተ ልብ ላይ የተጠበቀ ሆኖ አቆየዋለሁ አላቸው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“በእርሱ (በቁርኣን ንባብ) ልትቸኩል ምላስህን በእርሱ አታላውስ፡፡ (በልብህ ውስጥ) መሰብሰቡና ማንበቡ በእኛ ላይ ነውና፡፡ ባነበብነውም ጊዜ (ካለቀ በኋላ) ንባቡን ተከተል፡፡ ከዚያም ማብራራቱ በእኛ ላይ ነው፡፡” (ሱረቱል ቂያማህ 75፡16-18)፡፡
“እውነተኛው ንጉስ አላህም (ከሓዲዎች ከሚሉት) ላቀ፡፡ ወደ አንተ መወረዱም ከመፈጸሙ በፊት በማንበብ አትቸኩል፡፡ «ጌታዬ ሆይ! ዕውቀትንም ጨምርልኝ» በል፡፡” (ሱረቱ ጣሀ 20፡114)፡፡
6ኛ/ ቅዱስ ቁርኣን፡ በነቢያችን እና በሶሓቦች ልቦና ብቻ ሳይኾን የተቀመጠው፡ በጽሑፍም ተዘጋጅቶ ይቀመጥ ነበር፡፡ የአላህ መልክተኛ ነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በእጃቸው መጽሐፍም ሆነ በመጽሐፍ ላይ ያለን ነገር ማንበብ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ከአላህ ዘንድ አንድ የቁርኣን ሱራ ወይንም የተወሰነ አንቀጽ በሚወርድላቸው ጊዜ፡ ከሶሓቦቻቸው አንደኛቸውን በመጥራት፡ ይህንን አንቀጽ እንዲህ በሚባለው ሱራ ውስጥ፣ እንዲህ ተብሎ ከሚጠራው ሱራ ቀጥሎ አስቀምጡት (ጻፉት) በማለት ያዙ ነበር፡፡ ቀጣዩ ሐዲሥ ይህንን እውነታ እንዲህ ያብራራዋል፡-
وروى عثمان بن عفان -رضي الله عنه-: كَانَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ إِذَا أُنْزِلَ عَلَيْهِ الشَّيْءُ دَعَا بَعْضَ مَنْ يَكْتُبُ لَهُ فَيَقُولُ ضَعُوا هَذِهِ فِي السُّورَةِ الَّتِي يُذْكَرُ فِيهَا كَذَا وَكَذَا وَإِذَا أُنْزِلَتْ عَلَيْهِ الْآيَاتُ قَالَ ضَعُوا هَذِهِ الْآيَاتِ فِي السُّورَةِ الَّتِي يُذْكَرُ فِيهَا كَذَا وَكَذَا وَإِذَا أُنْزِلَتْ عَلَيْهِ الْآيَةُ قَالَ ضَعُوا هَذِهِ الْآيَةَ فِي السُّورَةِ الَّتِي يُذْكَرُ فِيهَا كَذَا. (رواه أحمد والحاكم، وحسنه الحافظ ابن حجر).
ዑሥማን ኢብኑ ዐፋን (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አንዳች የቁርኣን ክፍል በሚወርድላቸው ጊዜ፡ ከጸሐፊዎቹ አንዱን በመጥራት፡- ‹‹ይህንን አንቀጽ እንዲህ ተብሎ በሚጠራው ሱራ ውስጥ አስቀምጡት››፡፡ አሁንም በድጋሚ የተወሰኑ የቁርኣን አንቀጾች ሲወርድላቸው፡ ‹‹እነዚህን አንቀጾች እንዲህ ተብሎ በሚጠራው ሱራ ውስጥ አስቀምጡት›› ይሉ ነበር” (ሙስነድ ኢማሙ አሕመድ 499፣ ሐኪም አል-ሙስተድረክ 2875፣ 3272)፡፡
7ኛ/ ቅዱስ ቁርኣንን በአላህ ነቢይ ትእዛዝ የሚጽፉ የነበሩ የተወሰኑ ሶሓባዎች ነበሩ፡፤ እነዚህ ሶሓባዎች ‹‹ኩትታቡል-ወሕይ›› በመባል ይታወቃሉ፡፡ ዋና ዋናዎቹም፡- ሁለቱ ኹለፋኦች (ዑሥማን፣ ዐሊይ)፣ ዘይድ ኢብኑ-ሣቢት፣ አብባን ኢብኑ-ሠዒድ ኢብኑል-ዓስ፣ ኡበይ ኢብኑ-ከዕብ፣ አርቀም ኢብኑ-አቢ አል-አርቀም፣ ሙዓዊህ ኢብኒ አቢ-ሱፍያን፣ ኻሊድ ኢብኑል-ወሊድ፣ ረዲየላሁ ዐንሁም ናቸው፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡
እነዚህ የቁርኣን ጸሐፍት፡ ወቅቱ በፈቀደላቸው የጽሕፈት መገልገያ መሳሪያዎች፡- የዘንባባ ዛፍ ቅርፊት፣ ስስ ድንጋይ፣ የቆዳ ቁራጭ፣ ካርቶን፣ በግመል ላይ በሚቀመጠው ኮርቻ፣ የግመል/ የፍየል ሰፋፊ አጥንት ላይ ይጽፉ ነበር፡፡ ከዛም ለራሳቸው ኮፒ ጽፎ በማስቀረት፡ የጻፉትን በአላህ መልክተኛ ቤት ያኖሩት ነበር፡፡
ዘይድ ኢብኑ-ሣቢት (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “ነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘንድ እያለን፡ ቁርኣንን በዛፍ ቅርፊት ወይም በቆዳ ላይ እንጽፍ ነበር” (ቲርሚዚይ 4335)፡፡
ይህ በረሱል ሶለላሁ አለይሂ ወሰለም ዘመን፡ በልብ ተሐፍዞ፡ በዘመኑ የጽሕፈት መገልገያ መሳሪያዎች ላይ ተጽፎ የነበረው ቁርኣን፡ ወደ አንድ መጽሐፍ የመሰብሰቡ ሂደት ደግሞ፡ መቼ እና እንዴት እንደነበር በቀጣዩ ፕሮግራማችን ላይ በአላህ ፈቃድ እንመለከተዋለን ኢንሻአላህ፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


