ኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
በአንድ ወቅት ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ዚል-መጃዝ በተሰኘው የገበያ ማዕከል እለፉ፡- ‹እናንተ ሰዎች ሆይ! ላ ኢላሀ ኢለሏህ በሉ! ትድናላችሁና በማለት ተናገሩ፡፡ የከሀዲያን ቁንጮ የነበረው አቡ ጀህልም በሳቸው ላይ አፈርን እየበተነባቸው፡- እናንተ ሰዎች ሆይ! ይህ ሰው ከሃይማኖታችሁ እንዳያስታችሁ፡፡ እሱ የሚፈልገው አማልክቶቻችሁን እንድትተዉ ነው፡፡ ላትናና ዑዝዛን ከማምለክ እንድትቆጠቡ ነውና የሚፈልገው አትስሙት አላቸው፡፡ የአላህ መልክተኛም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ወደሱ ፊታቸውን ሳያዞሩ ዳዕዋቸውን ቀጠሉ፡፡ (ሙስነድ ኢማሙ አሕመድ 16119)፡፡
‹‹ላ ኢላሀ ኢለሏህ›› እንበል!
ብቸኛው የመዳኛ መስመር ነው፡፡ ከዚህ እምነት ውጪ የሆነ በጠቅላላ ዘላለማዊ ክስረት እንጂ ሌላ አይጠብቀውም፡፡ ‹ላ ኢላሀ ኢለሏህ› ማለት፡- ከአንድ አላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም ማለት ነው፡፡ አዎ! ሁላችንም የአንዱ አምላክ አላህ ፍጡሮች ነን፡፡ ሁለት አምላክ የለንም፡፡ የምናመልካቸው አማልክት መብዛታቸው አምላክን ከአንድነቱ አይቀይረውም፡፡
አንዱንና እውነተኛውን አምላክ አላህን ማምለክ የነቢያት በጠቅላላ (ሰላም በሁሉም ላይ ይሁን) ሃይማኖታዊ ስብከት ነው፡፡
“ከአንተ በፊትም፣ እነሆ ከኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ፣ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢሆን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።” (ሱረቱል አንቢያእ 25)፡፡
“በየሕዝቡም ሁሉ አውስጥ አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ፤ በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል…” (ሱረቱ-ነሕል 36)፡፡
“ከባሮቹ በሚሻው ሰው ላይ መላእክትን ከራእይ ጋር በፈቃዱ ያወርዳል፤ (ከሐዲዎችን በቅጣት) አስጠንቅቁ፤ እነሆ ከኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም ፍሩኝም ማለትን (አሳታውቁ በማለት ያወርዳል)።” (ሱረቱ-ነሕል 2)፡፡
ይህንን አስተምህሮ የሚቃወም ሰው እሱም ‹የዘመናችን አቡ-ጀህል› ይባላል፡፡ መላእክትን፣ ነቢያትን፣ ጻድቃንን፣ ሰማእታትን፣ ሙታንን፣ ግኡዛን ነገራትን በማምለክ በፍጹም ጀነት አይገኝም!!፡፡
የአላህ ነቢይም (ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም) ፡- ‹‹እነሆ ጀነትን ሙስሊም የሆነች ነፍስ እንጂ ሌላው አይገባትም›› አሉ፡፤ (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
“እላንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገቢዉን መጠንቀቅ ተጠንቀቁት፤ እናንተም ሙስሊሞች ሆናችሁ እንጅ አትሙቱ።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 102)፡፡
“በርሷም (በሕግጋቲቱ) ኢብራሂም ልጆቹን አዘዘ፡፡ ያዕቁብም (እንደዚሁ ልጆቹን አዘዘ)፡፡ «ልጆቼ ሆይ! አላህ ለናንተ ሃይማኖትን መረጠ፤ ስለዚህ እናንተ ሙስሊሞች ኾናችሁ እንጂ አትሙቱ» (አላቸው)፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 132)፡፡
“ጌታዬ ሆይ! ከንግስና በእርግጥ ሰጠኸኝ፤ ከሕልሞችም ፍች አስተማርከኝ፤ የሰማያትና የምድር ፈጣሪ ሆይ! አንተ በቅርቢቱና በመጨረሻይቱ ዓለም ረዳቴ ነህ፤ ሙስሊም ሆኜ ግደለኝ፤ በመልካሞቹም አስጠጋኝ፤ (አለ)።” (ሱረቱ ዩሱፍ 101)፡፡
“የጌታችንም ታምራቶች በመጡልን ጊዜ ከማመናችን በቀር ከኛ አትጠላም፤ ጌታችን ሆይ! በኛ ላይ ትግእስትን አፍስስ፤ ሙስሊሞች ሆነን ግደለን።” (ሱረቱል አዕራፍ 126)፡፡
የተውበት በሩ ከመዘጋቱ በፊት ሁላችንም ወደ አላህ መንገድ እንመለስ፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


