የእምዬን ወደ አብዬ!
ኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
” يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَسْأَلُوا عَنْ أَشْيَاءَ إِنْ تُبْدَ لَكُمْ تَسُؤْكُمْ وَإِنْ تَسْأَلُوا عَنْهَا حِينَ يُنَزَّلُ الْقُرْآنُ تُبْدَ لَكُمْ عَفَا اللَّهُ عَنْهَا وَاللَّهُ غَفُورٌ حَلِيمٌ * قَدْ سَأَلَهَا قَوْمٌ مِنْ قَبْلِكُمْ ثُمَّ أَصْبَحُوا بِهَا كَافِرِينَ ” سورة المائدة 102-101
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለእናንተ ቢገለጹ ከሚያስከፏችሁ ነገሮች አትጠይቁ፡፡ ቁርኣንም በሚወርድበት ጊዜ ከእርሷ ብትጠይቁ ለናንተ ትገለጻለች፤ ከእርሷ አላህ ይቅርታ አደረገ፡፡ አላህም መሓሪ ታጋሽ ነው፡፡ ከናንተም በፊት ሕዝቦች በእርግጥ ጠየቋት፡፡ ከዚያም በእርሷ (ምክንያት) ከሓዲዎች ኾኑ፡፡” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡101-102)፡፡
በዚህ አንቀጽ ላይ ከካፊሮች በኩል የቀረበ አንድ ጥያቄ አልለ፡፡ እሱም፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለእናንተ ቢገለጹ ከሚያስከፏችሁ ነገሮች አትጠይቁ›› የሚለውን ቆንጥሮ በማውጣት፡- ኢስላም ከተከታዮቹ ጥያቄን ማስተናገድ አይፈልግም፡፡ አማኞቹ ያለ-ምንም ጥያቄ ዝም ብለው እንዲከተሉ ስለሚፈልግ ‹‹አትጠይቁ!›› በማለት ከልክሏል! ይሉናል፡፡ የጳውሎስን እከክ በጀማል ላይ ልክክ! ይሏችኋል እንዲህ ነው፡፡ እኛም ለዚህ ጥያቄ መሳይ ተቃውሞ የሚኖረን ምላሽ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡ ወማ ተውፊቂ ኢልላ ቢልላህ፡-
ጥቅላዊ ምላሽ፡-
የቅዱስ ቁርኣኑ አንቀጽ ለማስተላለፍ የፈለገው ነገር፡ ሰዎች መሰረታዊ ያልኾነ፡ ከሕይወታቸው ጋር ተዛማጅነት የሌለው፡ ማወቁ የማይጠቅምና አለማወቁ የማይጎዳን ነገር እያነሱ በመጠየቅ ነቢያቸውን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዳያስቸግሩ የሚገስጽ ነው፡፡ እንዲሁም ከተአምራት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነገራት ይፈጸሙላቸው ዘንድ ጥያቄን ከማብዛት ይልቅ የታዘዙትን ለመፈጸም ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ለመምከር ነው፡፡ ያ ሳይኾን ቀርቶ፡ እነሱ የጠየቁት ተአምር ቢፈጸምላቸውና ኋላም ሳያምኑ ቢቀሩ ከዓለማት ማንም ያልተቀጣውን ቅጣት እንደሚቀጡ በማወቅ አርፈው ይቀመጡ ዘንድ ለመርዳት ነው፡፡ በተጨማሪም ሸሪዓው ግዳጅ (ዋጂብ) ነው ብሎ ሳይደነግግ በዝምታ ያለፋቸውን ነገራት፡ እነሱም ዝም ብለው ማለፍ ሲገባቸው፡ ጥያቄ እያበዙ በራሳቸው ላይ ተጨማሪ ግዳጆችን እንዳያስደነግጉና ኋላም ግዳጁን ለመወጣት እንዳይቸገሩ ለመርዳት ነው አትጠይቁ! የተባሉት፡፡ ከዚህ ውጭ ሃይማኖትን በተመለከተ ‹‹አትጠይቁ!›› የሚል ነገር ቃሉ ላይ አልተጻፈም፡፡
ዝርዝር ምላሽ፡-
1ኛ/ ኢስላም የዕውቀት ሃይማኖት ነው፡፡ እንደውም ሃይማኖቱ ከእምነት በፊት ዕውቀትን በማስቀደሙ ከወገኖቻችን ሃይማኖት አንዱ መለያው ነው፡፡ የሃይማኖቱ የመጀመሪያ መርሕ ‹‹ዕወቅ›› እንጂ ‹‹እመን›› አይደለም፡፡ ዕውቀት እራሱ ወደ እምነት ይጠራሀልና ቅድሚያ ለዕውቀት ስጥ ነው፡፡ ያላወቀ ሰው አመንኩ ቢል እንኳ፡ ስላመነው ነገር ሌሎችን ማስረዳት አይችልም፡፡ ጥያቄ ቢቀርብለት መመለስ አይችልም፡፡ ያወቀ ሰው ግን ባያምንበት እንኳ ስለ ጉዳዩ መናገር ይችላል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” فَاعْلَمْ أَنَّهُ لَا إِلَهَ إِلَّا اللَّهُ وَاسْتَغْفِرْ لِذَنْبِكَ وَلِلْمُؤْمِنِينَ وَالْمُؤْمِنَاتِ وَاللَّهُ يَعْلَمُ مُتَقَلَّبَكُمْ وَمَثْوَاكُمْ ” سورة محمد 19
“እነሆ ከአላህ ሌላ አምላክ አለመኖሩንም ዕወቅ፡፡ ስለ ስህተትህም ለምእመናንም ምሕረትን ለምን፡፡ አላህም መዘዋወሪያችሁን፣ መርጊያችሁንም ያውቃል፡፡” (ሱረቱ ሙሐመድ 47፡19)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ጌታ አላህ ከሱ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን እመን ወይንም መስክር ሳይኾን ያለው ‹‹ዕወቅ›› በማለት ነው ያዘዘው፡፡ ዕውቀት የሃይማኖቱ ቀዳሚ መርሕ ነውና፡፡ ኢማሙል ቡኻሪይ (194-256 ሂጅ.) ረሒመሁላህ፡ በኪታባቸው ‹ሶሒሕ አል-ቡኻሪይ›› ላይ ይህን አንቀጽ መሰረት በማድረግ ዕውቀት ከንግግርና ከሥራ በፊት ቀዳሚ መኾኑን ይገልጻሉ፡፡ (ሶሒሕ አል-ቡኻሪይ፡ ኪታቡል ዒልም፡ 10ኛ ባብ)፡፡
ከቅዱስ ቁርኣን ለመጀመሪያ ጊዜ የወረደው 96ኛው ሱራ ሱረቱል ዐለቅ ከ1-5 ያለው አንቀጽ ነው፡፡ ይህ አንቀጽም መልእክቱን ሲጀምር ‹‹አንብብ!›› በማለት ነው የጀመረው፡፡ ንባብ ሙሉ ሰው ለመኾን አንዱ ወሳኝ ነገር ነውና፡፡ የወረደው የአላህ ቃልም እንዲህ ይነበባል፡-
” اقْرَأْ بِاسْمِ رَبِّكَ الَّذِي خَلَقَ * خَلَقَ الْإِنْسَانَ مِنْ عَلَقٍ * اقْرَأْ وَرَبُّكَ الْأَكْرَمُ * الَّذِي عَلَّمَ بِالْقَلَمِ * عَلَّمَ الْإِنْسَانَ مَا لَمْ يَعْلَمْ ” سورة العلق 5-1
“አንብብ በዚያ (ሁሉን) በፈጠረው ጌታህ ስም፡፡ ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)፡፡ አንብብ፤ ጌታህ በጣም ቸር ሲኾን፤ ያ በብርዕ ያስተማረ፡፡ ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ ሲኾን፡፡” (ሱረቱል ዐለቅ 96፡1-5)፡፡
የአላህ ቃል የኾነው ቅዱስ ቁርኣን፡ ያላውቅናቸውንና ያልተረዳናቸውን ነገሮች የዕውቀት ባለቤቶች ዘንድ በመኼድ ጠይቀን መረዳት እንዳለብን ያሳስበናል፡፡ ይህም የሚያሳየው ኢስላም መጠየቅን ሲያበረታታ እንጂ፡ ሲያስጠነቅቅ አይደለም፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” وَمَا أَرْسَلْنَا مِنْ قَبْلِكَ إِلَّا رِجَالًا نُوحِي إِلَيْهِمْ فَاسْأَلُوا أَهْلَ الذِّكْرِ إِنْ كُنْتُمْ لَا تَعْلَمُونَ ” سورة النحل 43
“ከአንተም በፊት ወደእነሱ ወሕይን (ራእይን) የምናወርድላቸውን ሰዎችን እንጂ ሌላን አልላክንም፡፡ የማታውቁም ብትኾኑ #የዕውቀትን_ባለቤቶች_ጠይቁ፡፡” (ሱረቱ-ነሕል 16፡43)፡፡
” وَتَوَكَّلْ عَلَى الْحَيِّ الَّذِي لَا يَمُوتُ وَسَبِّحْ بِحَمْدِهِ وَكَفَى بِهِ بِذُنُوبِ عِبَادِهِ خَبِيرًا * الَّذِي خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ وَمَا بَيْنَهُمَا فِي سِتَّةِ أَيَّامٍ ثُمَّ اسْتَوَى عَلَى الْعَرْشِ الرَّحْمَنُ فَاسْأَلْ بِهِ خَبِيرًا ” سورة الفرقان 59-58
“በዚያም በማይሞተው ሕያው አምላክ ላይ ተመካ፡፡ ከማመስገንም ጋር አጥራው፡፡ በባሮቹ ኀጢኣቶችም ውስጠ ዐዋቂ በእርሱ በቃ፡፡ ያ ሰማያትና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ፣ ከዚያም በዐርሹ ላይ (ሥልጣኑ) የተደላደለ አልረሕማን ነው፡፡ #ከእርሱም_ዐዋቂን_ጠይቅ፡፡” (ሱረቱል ፉርቃን 25፡58-59)፡፡
ጃቢር ኢብኒ ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- ወደ ሰፈር(ጉዞ) ወጣን፡፡ ከኛ ውስጥ አንድ ሰው ድንጋይ አናቱን ፈነከተው፡፡ ደግሞም ሰውየው ኢሕቲላም (ጀናባ) ኾነ፡፡ ሰውየውም አብረውት የነበሩ ሶሓቦችን ‹‹ከውኃ ይልቅ ተየሙም ማድረግ የሚያስችለኝን ነገር ልታገኙልኝ ትችላላችሁን?›› በማለት ጠየቀ፡፡ እነሱም፡- ‹‹አንተ ውኃን መጠቀም እስከቻልክ ድረስ፡ ወደ ተየሙም የሚወስድህን ፈቃድ አናገኝልህም›› በማለት መለሱለት፡፡ ሰውየውም ውኃን በመጠቀም ታጠበ ወዲያውኑም ሞተ፡፡ ወደ አላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ዘንድ በተመለስን ጊዜም ይህን ነገር ስንነግራቸው፡ እሳቸውም፡- ‹‹ገደሉት! አላህ ይግደላቸው! የማያውቁ ከኾነ አይጠይቁም ነበርን? #የመሃይም_መድኃኒቱ_መጠየቅ_ብቻ_ነው! እሱ በተየሙም ቢጠቀም ይበቃለት ነበር›› በማለት መለሱ፡፡ (አቡ ዳዉድ 336፣ ኢብኑ ማጀህ 615፣ አሕመድ 3112፣ ዳረቁጥኒይ 744)፡፡
2ኛ/ በጌታ አላህ ቃል ‹በቅዱስ ቁርኣን› ውስጥ፡ በወቅቱና በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የሚጠይቁዋቸው የነበሩ አንዳንድ ጥያቄዎችን ጌታ አላህ በቀጥታ በቁርኣኑ በኩል ምላሽን በመስጠት ቃሉን በመልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) አማካኝነት ያስተላልፍ ነበር፡፡ ይህም ኢስላም ጠይቆ መረዳትን የሚያበረታታ እምነት መኾኑን በግልጽ የሚያስረዳ ነው፡፡ የተወሰኑትን ለናሙና እንመልከታቸው፡፡ ቦታ ላለማጣበብም የአማርኛውን ትርጉም ብቻ አቀርበዋለሁ፡-
“ባሮቼም ከእኔ በጠየቁህ ጊዜ (እንዲህ በላቸው)፡- እኔ ቅርብ ነኝ፡፡ የለማኝን ጸሎት በለመነኝ ጊዜ እቀበለዋለሁ፡፡ ስለዚህ ለኔ ይታዘዙ፤ በኔም ይመኑ፤ እነሱ ሊመሩ ይከጀላልና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡186)፡፡
“(ሙሐመድ ሆይ!) ከለጋ ጨረቃዎች (መለዋወጥ) ይጠየቁሃል፡፡ እነርሱ ለሰዎች ጥቅም ለሐጅም (ማወቂያ) ጊዜያቶች (ምልክቶች) ናቸው በላቸው…” (ሱረቱል በቀራህ 2፡189)፡፡
“ምንን (ለማን) እንደሚለግሱ ይጠይቁሃል፡፡ ከመልካም ነገር የምትለግሱት፤ ለወላጆችና ለቅርብ ዘመዶች፣ ለየቲሞችም፣ ለድሆችም፣ ለመንገደኞችም ነው፡፡ ከበጎ ነገርም ማንኛውንም ብትሠሩ አላህ እርሱን ዐዋቂ ነው በላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡215)፡፡
“አእምሮን ከሚቃወም መጠጥና ከቁማር ይጠይቁሃል፡፡ «በሁለቱም ውስጥ ታላቅ ኃጢኣትና ለሰዎች ጥቅሞች አሉባቸው፡፡ ግን ኃጢኣታቸው ከጥቅማቸው በጣም ትልቅ ነው» በላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡219)፡፡
“ከወር አበባም ይጠይቁሃል፡፡ እርሱ አስጠያፊ ነው፡፡ ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው፡፡ ንጹሕ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቡዋቸው፡፡ ንጹሕ በኾኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኙዋቸው፡፡ አላህ (ከኃጢኣት) ተመላሾችን ይወዳል፤ ተጥራሪዎችንም ይወዳል በላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡222)፡፡
“ከሩሕም ይጠይቁሃል፡፡ «ሩሕ ከጌታዬ ነገር ነው ከዕውቀትም ጥቂትን እንጂ አልተሰጣችሁም» በላቸው፡፡” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡85)፡፡
“ሰዎች ከሰዓቲቱ ይጠይቁሃል፡፡ «ዕውቀትዋ አላህ ዘንደ ብቻ ነው፤» በላቸው፡፡ የሚያሳወቅህም ምንድን ነው! ሰዓቲቱ በቅርብ ጊዜ ልትኾን ይከጀላል፡፡” (ሱረቱል አሕዛብ 33፡63)፡፡
እነዚህ ለናሙና የቀረቡ ምሣሌዎች ናቸው፡፡ በውስጣቸውም፡- ሰዎቹ በወቅቱ ለሚያነሱት ጥያቄዎች ምላሽን ይሰጣቸው እንደነበረ ማብራሪያን ይዘዋል፡፡ ታዲያ በምን ሂሳብ ነው ኢስላም ጥያቄን አይወድም! የሚል ሂስ የሚሰነዝሩት?
3ኛ/ ኢስላም በጥያቄና መልስ የሚያምን ሃይማኖት ለመኾኑ ሌላው ማስረጃችን ተጨባጩ የሙስሊሞች ሕይወት ነው፡፡ በሁሉም ሀገር ቋንቋዎች የሚተላለፉ የኾኑ ኢስላማዊ የሳተላይት ጣቢያዎችን ብትመለከቷቸው፡ ሁሉም ለራሳቸው ሕዝቦች በገዛ ቋንቋቸው የሚተላለፍ አንድ ፕሮግራም አልለ፡፡ እሱም ‹‹አል-ፈታዋ›› የተሰኘው ዓምድ ነው፡፡ በዚህ ዓምድ ሙስሊሞች ካሉበት ቦታ ኾነው ወደ ፕሮግራም አዘጋጆች በቀጥታ በመደወል፡ ማንኛውንም አይነት ኢስላማዊ ጥያቄዎችን፣ ከሕይወታቸው ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ነገራት በጥያቄ መልክ ያቀርባሉ፡፡ ስለ አለባበስ፣ ስለ አመጋገብ፣ ስለ ንግድ፣ ስለ ፖለቲካ፣ ስለ ወላጅ ሐቅ፣ የዝምድና ሐቅ፣ የጎረቤት ሐቅ፣ ስለ ማኃበራዊ ኑሮ፣ ስለ ሐላልና ሐራም የሥራ ዘርፎች ወዘተ ጥያቄዎች በየጊዜው ይጎርፋሉ፡፡ ጥያቄው የሚቀርብለት ዓሊምም ያወቀውን በተረዳው መልኩ ያብራራል፡፡ አፍሪካ ቲቪ የተሰኘውን ብቸኛው ጣቢያችንን እንኳ (አላህ ይጠብቀው) ለአብነት ብንወስድ በውስጡ በኦሮሚኛ፣ አማርኛና ትግርኛ ቋንቋዎች የፈትዋ ዓምድ አላቸው፡፡ ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ ትፈልጋላችሁ ታዲያ?
የክርስቲያን የሳተላይት ጣቢያዎችን ስናይ የነሱን ሃይማኖታዊ ስብከትና ትምሕርት ብቻ ነው የምናዳምጠው!፡፡ የታለ የፈታዋ (ምን እንጠይቅልዎ) ፕሮግራሙ? አንድ ክርስቲያን በባንክ ተቀጥሮ ስለ መሥራት፣ ወለድ ስለመብላት፣ በወለድ የሚሰራ ባንክን በማኃበር ስለመክፈት፣ ስለ ሙዚቃና ስለ ዘፈን ሐራምነት ስለ ሃይማኖታዊ አለባበስ ስርአት የምትጠየቁበትና የምትመልሱበት የአየር ጊዜ መች አላችሁና? ወይስ ‹‹ኢየሱስ ጌታ ነው!›› ከሚለው ቃል ሌላ (አስተግፊሩላህ) ህዝቡ ምንም እንዳይሰማ ነው የሚፈለገው? እስኪ ማነው ጥያቄ ከተከታዮቹ እንዳይነሳበት የሚፈራው እምነት?
4ኛ/ እውነታው ከላይ እንዳየነው ኢስላም የዕውቀት፣ የምርምርና የልጠየቅ ልመልስ ሃይማኖት መኾኑን ከተረዳን፡ ‹ወገኖቻችን ከላይ ያነሱት የሱረቱል ማኢዳህ 5፡101-102 ትክክለኛው ፍቺ ምንድነው ታዲያ ወደሚለው ዝርዝር ምላሽ እንሂድ፡፡ ይህ አንቀጽ ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የወረደበት ብዙ ሰበቦችን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ እነዛን ምክንያቶች ማወቁ ለመልሱ አጋዥ ስለሚኾን፡ አንቀጹ የወረደበትን አንድ ሰበብ እንመልከት፡-
عَنْ عَلِيٍّ ، قَالَ : لَمَّا نَزَلَتْ هَذِهِ الآيَةُ : {وَلِلَّهِ عَلَى النَّاسِ حِجُّ الْبَيْتِ مَنِ اسْتَطَاعَ إِلَيْهِ سَبِيلاً} ، قَالُوا : يَا رَسُولَ اللهِ ، أَفِي كُلِّ عَامٍ ؟ فَسَكَتَ ، فَقَالُوا : أَفِي كُلِّ عَامٍ ؟ فَسَكَتَ ، قَالَ : ثُمَّ قَالُوا : أَفِي كُلِّ عَامٍ ؟ فَقَالَ : لاَ ، وَلَوْ قُلْتُ : نَعَمْ ، لَوَجَبَتْ فَأَنْزَلَ اللَّهُ تَعَالَى : {يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لاَ تَسْأَلُوا عَنْ أَشْيَاءَ إِنْ تُبْدَ لَكُمْ تَسُؤْكُمْ} إِلَى آخِرِ الآيَةِ. رواه أحمد في مسنده 917.
ዐሊይ ኢብኑ አቢ-ጧሊብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “‹‹ ለአላህም በሰዎች ላይ ወደርሱ መኼድን በቻለ ሁሉ ላይ ቤቱን መጎብኘት ግዴታ አለባቸው፡ ›› የሚለው አንቀጽ በወረደ ጊዜ፡ ሶሓቦችም ‹‹የአላህ መልክተኛ ሆይ! በየዓመቱ ነውን?›› ብለው ሲጠይቁ፡ እሳቸውም ዝም አሉ፡፡ እነሱም በድጋሚ፡- ‹‹በየዓመቱ ነውን?›› ሲሉ ዝም ተባሉ፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ጥያቄውን በመድገም ‹‹በየዓመቱ ነውን?›› ሲሉ፡ የአላህ መልክተኛም፡ ‹‹አይደለም! አዎ ብያችሁ ቢኾን ኖሮ፡ ግዳጅ ይኾንባችሁና እናንተም አትችሉም ነበር›› በማለት መለሱ፡፡ ወዲያውኑ አላህም፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለእናንተ ቢገለጹ ከሚያስከፏችሁ ነገሮች አትጠይቁ›› የሚለውን አንቀጽ አወረደው” (ሙስነድ ኢማሙ አሕመድ 917)፡፡
ከዚህ ሐዲሥ በግልጽ እንደምንረዳው፡- ሰዎቹ አላህ በናንተ ላይ ሐጅን ግዳጅ አድርጎባችኋልና፡ ግዳጃችሁን ፈጽሙ! ተብለው ከታዘዙ፡ ሰምተናል ታዘንማል በማለት ቀጥታ ግዳጅ የተደረገባቸውን ነገር በአላህ እገዛ ለመፈጸም መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ነው፡፡ እነሱ ግን ‹‹በየዓመቱ ነውን?›› በማለት ሌላ ጥያቄን አስከተሉ፡፡ በየዓመቱ ማድረግ ግዳጃቸው ቢኾን ኖሮ፡ ከመነሻውም አላህ ይነግራቸው ነበር፡፡ ለነሱ እዝነት ተብሎ በዝምታ ሲታለፍላቸው፡ የታዘዙትን ከመፈጸም ይልቅ፡ ያልታዘዙትን ነገር በመፈላፈል በየዓመቱ ነው ወይ የምናደርገው? ብሎ መጠየቃቸው አግባብ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም፡ በጥያቄያቸው መሰረት ‹አዎን!› የሚል ምላሽ ቢሰጣቸው ኖሮ ጉዳዩ ከአቅም በላይ ኾኖ ይከብዳቸውና ጭራሹንም ህጉን በመተው ኃጢአት ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡ ለዚህ ነው ኋላ ላይ ከአቅም በላይ ኾኖ እንዳይከፋችሁ፡ ከወዲሁ ባልታዘዛችሁት ነገር ላይ ጥያቄን በማንሳት አታብዙ የተባሉት፡፡
ከኛ የሚጠበቀው የታዘዘውን በአግባቡ መፈጸም እንጂ፡ ጥያቄ በማብዛት በራሳችን ላይ ግዳጅን መጫንና ኋላ ለመፈጸም ሲከብደን ሕጉን ተመልሰን በመካድ ከአጥፊዎች ለመኾን አይደለም፡፡ ቀጣዩ ሐዲሥም ጉዳዩን የበለጠ ያብራራዋል፡-
عَنْ أَبِى ثَعْلَبَةَ الْخُشَنِىِّ قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- « إِنَّ اللَّهَ عَزَّ وَجَلَّ فَرَضَ فَرَائِضَ فَلاَ تُضَيِّعُوهَا وَحَرَّمَ حُرُمَاتٍ فَلاَ تَنْتَهِكُوهَا وَحَدَّ حُدُودًا فَلاَ تَعْتَدُوهَا وَسَكَتَ عَنْ أَشْيَاءَ مِنْ غَيْرِ نِسْيَانٍ فَلاَ تَبْحَثُوا عَنْهَا. رواه الدارقطني 4445
ከአቢ ሠዕለበህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ኃያሉ አላህ ግዴታዎችን ደንግጓልና አታባክኑአቸው (ፈጽሙ)፣ ሐራም ነገራትንም ከልክሏልና አትጣሷቸው (አትዳፈሩ)፣ ድንበርን አበጅቷልና ወሰንን አትለፉ፣ አንዳንድ ነገራትን ደግሞ ረስቶ ሳይኾን ለናንተው በማዘን በዝምታ አልፏቸዋልና፡ ስለነሱ አትፈላፈሉ (አጥብቃችሁ አትጠይቁ)” (ዳረቁጥኒይ 4445)፡፡
ከዚህ በፊት የነቢዩላህ ሷሊሕ (ዐለይሂ-ሰላም) ሕዝቦች፡ ነቢያቸውን ሷሊሕን፡ አላህ ግመልን ከቋጥኝ ስር እንዲያወጣላቸው፡ የሱንም ነቢይነት አረጋግጠው እንዲያምኑ በመፈለግ ጥያቄን አቀረቡለት፡፡ እሱም ጌታውን አላህ በመለመን፡ ለነቢይነቱ ምልክት የምትኾነው ግመልም ተሰጠችው፡፡ ከተአምሩ በኋላ ግን፡ የሷሊሕ ሕዝቦች እንኳን ሊያምኑ፡ ግመሊቷንም በመውጋት ገደሏት፡፡ ከመጨረሻው ዓለም (ከአኼራ) ቅጣት በፊትም በዱንያ ቅጣት አላህ አጠፋቸው (ሱረቱ ሁድ 11፡64-68፣ ሱረቱ-ሹዐራእ 26፡141-159፣ ሱረቱ-ሸምስ 93፡11-15)፡፡ የማይፈጽመውን ነገር በመጠየቅ እራሱ ላይ ግዳጅን ያመጣና ኋላም ኃጢአት ውስጥ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ ነው መልእክቱ!!
በዚህ ዙሪያ የቅዱስ ቁርኣን ተንታኞችን (ሙፈሲሮች) ማብራሪያ በማቅረብም ብዙ ማለት ይቻል ነበር፡፡ ግን ጽሑፍ መብዛቱ (ይህም በዝቷል) አንባቢን ስለሚያሰለች፡ በዚህ ላብቃ፡፡ አላህ የበለጠውን እውነታ ዐዋቂ ነው፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


