❝…ክርስቲያን መሆንህን (መክፈርህን) ይፋ ሳታደርግ ሙስሊም መስለህ አብረሀቸው በመስገድና በመጾም ቀስ በቀስ ወንጌልን ስበካቸው…❞
ከአመታት በፊት ጋዜጠኛ አብዱረሒም ቢቢኤን ሬዲዮ ላይ በሚሰራበት ወቅት አንድ ማንነቱ ከማይታወቅ ሰው ሚስጥራዊ ቪዲዮ ተላከለት። የዚህ ቪዲዮ ¹ ይዘት አስደንጋጭ ነበርና ይፋ ከማድረጉ በፊት የተወሰነ ቀን አሰበበት፥ ለሚቀርባቸውም ሰዎች አጋርቶት ተማከረበት። በስተመጨረሻም ይፋ አደረገው። ይፋ ከተደረገ በኃላ ብዙውን ሰው አስደነገጠ፣ መነጋገርያም ሆነ። ቪዲዮውን ለማስታወስ ያክል አንድ የሙስሊም አለባበስ የለበሰ ሰው የሆነ መጋዘን ውስጥ ለወንጌላውያን የሰጡትን ተልዕኮ እንዴት እየፈጸመ እንዳለ በዝርዝር የሚተነትንበት ነው።
ግለሰቡ ጀለብያና መሠል የሙስሊም አልባሳትን በመልበስ በመስጅዶች በመገኘት ማንም እንዳይጠረጥረው ዒባዳዎችን በመፈጸም በመሀል የተወሰኑ ሰዎችን ከቀረበ በኃላ ቀስ እያለ ወንጌልን የሚሰብክበት መንገድ ነው። በዚህ ስራ ውስጥ ብዙ ቦታዎችን ያካለለ ሲሆን አንዳንዴ እንደተሳካለት አንዳንዴ ደግሞ ነቅተውበት እንዳባረሩት በቪዲዮው ላይ ይዘረዝራል። ይህንን ታሪክ ሲሰማ አንዳንድ ሰው ተራ የተጋነነ ቀልድ ሊመስለው ይችላል። ከአስርተ አመታት በፊት የተጻፉ የሚሽነሪዎችን ጥናት ለተመለከተ ሰው ግን ግለሰቡ ቃል በቃል በማኑዋሎቻቸው መሠረት ተግባሩን እንደፈጸመው ይረዳል። ከዚህ በታች የተወሰኑትን እየጠቀስኩ አስቃኛችኃለው።

ከዛሬ 40 አመት ገደማ በፊት በጄምስ ላንግፎርድ ለማስተርስ መመረቂያ የተጻፈው “Some Principles of Christian Mission to Muslims” የተሰኘው ጥናት ይህንን በተመለከተ በዝርዝር ጽፏል። መጽሀፉ በገጽ 160 “ENCOURAGE MUSLIM CONVERT TO REMAIN IN HIS COMMUNITY” በሚል ርዕስ ስር አንድ ክርስትናን የተቀበለ ሰው የሙስሊም ሀይማኖታዊ ድንጋጌዎች ሳይቀር እየፈጸመ በራሱ ማኅበረሰብ ውስጥ ቆይቶ በድብቅ መስበኩ ጥሩ ውጤት እንደሚያመጣ ይገልጻል።
በተመሳሳይ ፓርሻል “Evangelizing Muslims: Are There Ways?” በሚል ርዕስ በጃንዋር 1979 በጻፈው ጹሁፉ የከፈሩ ሰዎች ቦታቸውን ለቀው ከሚሔዱ ይልቅ በአካባቢው ቆይተው በሒደት መስበክ ቢችሉ የተሻለ ብዜት የሚፈጥሩ እነሱ እንደሆኑ ያትታል ❝ Most of the “reproduction” has been done by converts themselves❞
ሲጠቃለል
መሠል ጉዳዮች ለአንድ ሙስሊም ለማሰብ እራሱ የሚከብዱና ይኖራል ብሎ የማይገምታቸው ቢሆንም በሚሽነሪው አለም ግን እውን ሁነው የታዩ ናቸው። የኩፍሩ አለም ሙስሊሙን ከእምነቱ ለማስወጣት ማንኛውንም መስዋዕትነት የሚከፍል ሲሆን ለዚህ ተግባሩ ደግሞ መርህ የሚባል ነገርን አያውቅም። የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው በሚለው ብሒል መዳረሻውን ብቻ የተመለከተና መንገዶቹ የፈለገ ከእምነቱና ከህሊናው ጋር እንኳን ቢጋጩ ግን የማይሰጡት ነው።
_________
¹ https://youtu.be/1jXrLaK0Qcg


