(የሕያ ኢብኑ ኑህ)
የአላህ መልዕክተኛ (ሰዐወ) ሲናገሩ
ﺇِﺫَﺍ ﻗَﺎﺗَﻞَ ﺃَﺣَﺪُﻛُﻢْ ﺃَﺧَﺎﻩُ ﻓَﻠْﻴَﺠْﺘَﻨِﺐْ ﺍﻟْﻮَﺟْﻪَ ﻓَﺈِﻥَّ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﺧَﻠَﻖ ﺁﺩَﻡَ ﻋَﻠَﻰ ﺻُﻮﺭَﺗِﻪِ
“When any one of you fights with his brother, he should avoid his face for Allah created Adam in his [or His own] image.” (Sahih Muslim, Hadith 4731)
“አንደኛችሁ ከወንድሙ ጋር ሲጣላ፥ ፊቱን ይቆጠብ (ከመምታት)። አሏህ አደምን የፈጠረው በምስሉ ነውና“ ሰሒሕ ሙስሊም 4731
ይህንን ሀዲስ አስመልክቶ አንዳንድ ክርስቲያኖች የዘፍጥረቱን አንቀፅ በማሰብ “አደም በአላህ አምሳያ” ተፈጠረ ማለቱ እኛ የአምላክ ምስልንና ቅርፅን ይዘን መገኘታችንን ያሳያል ሲሉ ሊያቀርቡ ይሞክራሉ፡፡
ከዚህ በታች “… አላህ አደምን የፈጠረው በራሱ ምስል ነው” የሚለውን ሀሳብ አስመልክቶ ዝርዝር ማብራሪያዎችን አስቀምጣለሁ፡፡
ሀዲሱን አስመልክቶ ኢማም ነወዊ ( ሞ. 676) ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ
“ሙስሊም ሊቃውንት ሀዲሱን አስመልክቶ የተለያዩ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል ከነዚህም መካከል “በራሱ ምስል” ማለት በሚጣላው ወንድሙ ምስል ማለቱ ሲሆን የሙስሊምን ሀዲስ እንደመረጃነት ያጣቅሳሉ፤ ሁለተኛው ደግሞ በራሱ በአደም ምስል ማለትም የቃሉ ባለቤቱ አደም ነው የሚሉ ሲሆን ይህኛው ደካማው አመለካከት ነው፡፡ የመጨረሻው ማብራሪያ ደግሞ በአላህ ምስል የሚለው ሲሆን ይህ ማለት ግን አካላዊ መመሳሰልን በሚገልፅ ሁኔታ ሳይሆን አደምን ወደ አላህ አስጠግቶ የማክበር ገለፃን የያዘ ነው፤ ይህም ለአብነት “የአላህ ግመል” እንዲሁም “የአላህ ቤት” እንደተባሉ መሠል ገለፃዎች ማለት ነው.! ወሏሁ አዕለም” (ሸርህ አነወዊ 8/440)
በዚህም ሀዲሱን አስመልክቶ ሊሰጡ የሚችሉ ሶስት ማብራሪያዎችን እንመለከታለን
1/ ሀዲሱ እንደሚገልፀው አንድ ሰው የወንድሙን ፊት ከመምታት መቆጠብ ይኖርበታል፤ ምክንያቱም አላህ አደምን በዚህ ሰውየ መልክ ነው የፈጠረውና..! እንደ ኢማም ነወዊ ገለፃ ይህኛው ማብራሪያ በመረጃ የታገዘ ነው፡፡
2/ ሁለተኛው ማብራሪያ አላህ አደምን የፈጠረው በራሱ በአደም ቅርፅ ነው የሚለው ሲሆን ይህም ለአደም ባዘጋጀው የቅርፅ ልክ አደም መፈጠሩን የሚገልፅ ነው፤ አንቀፁ በዚህ መልኩም መብራራት የሚችል ሲሆን ለኢማም ነወዊ ግን የመጀመሪያው የተሻለ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
3/ ሶስተኛውና የመጨረሻውው ገለፃ ባለቤቱን/Subject/ አላህ በማድረግ የተብራራበት መንገድ ነው፡፡ ይህም የሰውን ልጅ ከፍጥረታት ነጥሎ ወደ አላህ በማስጠጋት የማላቅና የማክበር ሁኔታ ነው፡፡ ይህን አገላለፅ ቁርዓን ውስጥ እናገኘዋለን፡፡
ለአብነትም
ሀ) የአላህ ግመል – ይህች ግመል የአላህ ግመል ናት ማለት አላህ የሚገለገልባት እንስሳ ናት ማለት አይደለም፤ ይልቁንስ ከግመሎች የተለየችና ለተዓምር የተፈጠረች ልዩ ግመል መሆኗን አፅንኦት ለመስጠት የገባ ቃል ነው፡፡
ለ) የአላህ ቤት – ይህ አገላለፅም አላህ ማረፍያና ማደሪያ ቤት አለው የሚል መልዕክት ያለው ሳይሆን፤ በምድር ካሉ ማምለኪያ ስፍራዎች ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው ቅዱስ ስፍራ መሆኑን ለመጠቆም ነው (ዘፍጥረት 28:19 በተመሳሳይ «ቤቴል» ብሎ ያስቀምጠዋል)
በዚህም የአደም ልጅ ከአላህ ማንነት ጋር ተያይዞ መነሳቱ ልክ እንደ ግመሏና እንደ አላህ ቤት እሱም ከተፈጠሩ ፍጡራን ሁሉ ለአላህ ቅርብና የተከበረ ባሪያ መሆኑን ለመጠቆም የገባ ቃል ነው፡፡ ይህን ሀሳብ ይበልጥ የሚያብራራልን የሚቀጠለው ሀዲስ ነው፦
ኢብን አባስ ባስተላለፉት ሀዲስ የአላህ መልዕክተኛ (ሰዐወ) በአንድ ወቅት ወደ ካዕባ ፊታቸውን አዙረው እንዲህ አሉ፦
“የተባረከው የአላህ ቤት፣ ምንኛ ታላቅ ነህ መብትህስ ምንኛ የገዘፈ ነው፤ ግና በአላህ ፊት የሙዕሚን መብት ካንተ ይበልጣል” (ሹዑቡል ኢማን ሀዲስ 3853)
ታዲያ ካለምንም የህሊና ማመሳሰል ካዕባ የአላህ ቤት ከተባለ ከካዕባ የላቀ ክብር ያለው የሰው ልጅ ተመሳሳይ አገላለፅ ቢቸረው ምን ጥያቄ ይፈጥራል? ሙስሊም ምሁራን በአብዛኛው ይህንን ማብራሪያ የተከተሉ ሲሆን የሚሽካት አል መሳቢህን ጥራዝ የተረጎሙት ዶ/ር ጄምስ ሮብሶን ተመሳሳይ ማብራሪያን ተጠቅመዋል፡፡
ጥያቄውን አስመልክቶ ግን ሶስቱም ማብራሪያዎች የማያዳግም ምላሽ ይሰጡታል..! የተነሱበትን ሀሳብ ሊያብራራ የሚችል ምንም አይነት ኢስላማዊ የሰነድና የገለፃ ድጋፍም የላቸውም፡፡
ወሏሁ አዕለም..!
በዚህ ዙሪያ ኡስታዝ ኢልያህ ማሕሙድ በድምፅ የሰጠውን ተጨማሪ ማብራሪያ ለማዳመጥ ይህንን ይጫኑ


