ኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ውዳሴና ሰላም የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለኾኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ታሀ 47)፡፡
ባለፈው ትምሕርታችን ላይ ስለ ቅዱስ ቁርኣን አመጣጥ የተወሰነ ነገር ተመልክተን ነበር፡፡ በውስጡም፡- ቁርኣን የአላህ ቃል መኾኑን፣ የተወረደው በዐረብኛ ቋንቋ መኾኑን፣ በመልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) አማካኝነት የወረደ መኾኑን፣ በጠቅላላ አንድ ጊዜ ሳይኾን 23 ዓመታት በፈጀ ጊዜ ውስጥ እንደ አስፈላጊነቱ ተከፋፍሎ መውረዱን፣ በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ትእዛዝ፡ እሳቸው በሕይወት እያሉ፡ ወቅቱ በፈቀደው የጽሕፈት መገልገያ መሣሪያ አማካኝነት በሶሓቦች (ረዲየላሁ ዐንሁም) መጻፉን ተመልክተናል፡፡ ይህ ትምሕርት ያልደረሰው ሰው ተከታዩን ሊንክ በማስፈንጠር ማንበብ ይችላል፡፡ ይጫኑ
ዛሬ የምንመለከተው ደግሞ፡- ይህ የአላህ ቃል የኾነው ቁርኣን እንዴት ተሰብስቦ አንድ መጽሐፍ እንደኾነ፡ እሱም በማን ጊዜ እንደተሰበሰበ እና ለዚህም ምክንያቱ ምን እንደነበር እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡፡ መልካም ንባብ፡-
1ኛ/ ቅዱስ ቁርኣን በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የሕይወት ዘመን፡ ከአላህ ዘንድ ወደሳቸው ልብ ወርዶ፣ በሳቸውና በተወሰኑ ሶሓቦች ልብ በቃል የተያዘ ኾኖ፣ እንዲሁም በጽሑፍ ተገልብጦ የተጠናቀቀ ቢኾንም፡ ያ በልብ የተያዘውና በእጅ የተጻፈው ቁርኣን ተሰብስቦ አንድ መጽሐፍ ኾኖ አልተዘጋጀም ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ፡-
ሀ/ የወሕይ አለመቋረጥ (አለመጠናቀቅ)፡- የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከአላህ ዘንድ በመልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ ሰለም) አማካኝነት ይወርድላቸው የነበረውን ቁርኣን በየጊዜው ይጠባበቁ ነበር፡፡ ከቁርኣን ሱራዎች የአንዱ ሱራ የተወሰነ አንቀጽ ይወርድላቸውና፡ ይህ የቁርኣን ሱራ ክፍል ሙሉ በሙሉ ወርዶ ከመጠናቀቁ በፊት፡ በቀጣዩ ደግሞ የሌላ ሱራ ክፍል የኾነው የተወሰነ የቁርኣን አንቀጽ ይወርዳል፡፡ በመቀጠልም መጀመሪያ ላይ ወርዶ የነበረው ቀሪው የቁርኣን ሱራ ክፍል ይወርድና ሱራው ይጠናቀቃል፡፡ ከዚያም የሌላ ሱራ አናቅጽ ወይንም ሙሉ ሱራ ይወርዳል፡፡ ቁርኣን የተሟላ ኾኖ እስኪጠናቀቅ ድረስ በዚህ መልኩ ነበር የወረደው፡፡ ይህ ደግሞ ቁርኣን ሰብስቦ በሱራዎቹ ቅደም ተከተል መሠረት ለመሰብሰብ አይመችም ነበር ማለት ነው፡፡ (ሙጀዝ ዑሉሚል-ቁርኣን 159፣ ዘርከሺይ፡ አል-ቡርሀን ፊ ዑሉሚል ቁርኣን 1/262)፡፡
ለ/ የአወራረዱ ቅደም ተከተል፡- የቅዱስ ቁርኣን የሱራዎቹና የአንቀጾቹ አቀማመጥና ቅደም ተከተል፡ በአወራረዱ መሠረት አልነበረም፡፡ አንዳንድ የቁርኣን ሱራዎች በአወራረድ ቅደም ተከተል መጀመሪያ አካባቢ ላይ የወረዱ ኾነው፡ በቁርኣን ላይ ሲቀመጡ ግን ወደ መጨረሻ ላይ ይኾናል ተራቸው፡፡ ለምሣሌ፡- 96ኛው ሱራ ‹‹ሱረቱል-ዐለቅ›› ከ1-5 ያለው አንቀጽ፡ ከቁርኣን ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ የወረደ ነው፡፡ ዛሬ ግን በቁርኣን ውስጥ አቀማመጡ ከ95 ሱራዎች በኋላ 96ኛ ረድፍ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ እንዲሁም 2ኛውን ሱራ ‹‹ሱረቱል-በቀራህን›› ብንመለከተው፡ በመዲና ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወረዱት ሱራዎች ነው፡፡ ግን በቁርኣን ውስጥ መጀመሪያዎቹ ተርታ ከፋቲሓ ቀጥሎ በ2ኛ ምእራፍ ላይ ነው የተቀመጠው፡፡ ቁርኣን እንደ አወራረዱ ቅደም ተከተል ቢኾን ኖሮ የተጻፈው፡ የምእራፎቹ ቅደም ተከተል፡ ቀድሞውኑ በለውኸል መሕፉዝ (በተጠበቀው ሰሌዳ) ከተቀመጠው ጋር የተቃረን ነበር የሚኾነው፡፡ በዚህም ሰበብ ቁርኣንን እሳቸው በሕይወት እያሉ፡ ለውኸል-መሕፉዝ ላይ ባለው አቀማመጥ ቅደም ተከተል መሠረት መሰብሰቡ አልተመቸም ማለት ነው፡፡ (ዶክተር. ጀማል ሙስጣፋ ዐብዲል-ሓሚድ፡ ጀምዑል ቁርኣን በይነል ሓቃኢቂ-ሣቢተቲ ወሽ-ሹቡሓት አል-ሃቢጠህ 43)፡፡
ሐ/ የመልክተኛው ቆይታ ማጠር፡- ረሱል (ሶለላሁ አለይሂ ወሰለም) ቁርኣን በሳቸው ላይ ተጠናቅቆ ከወረደ በኋላ፡ በሕይወት የቆዩት ለጥቂት ቀናት ነው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፡ ከቁርኣን ለመጨረሻ ጊዜ የወረደው በሱረቱል በቀራህ አንቀጽ 281ኛው ላይ የሚገኘው የቁርኣን አንቀጽ ነው፡፡ ከዚህ የቁርኣን አንቀጽ መውረድና የወሕይ መጠናቀቅ በኋላ በሕይወት የቆዩት ለዘጠኝ ቀናት ያህል ነው፡፡ በነዚህ ቀናት ውስጥ ደግሞ ሙሉውን ቁርኣን በአንድ መጽሐፍ ለመሰብሰብ በቂ ጊዜ አልነበረም፡፡
መ/ የሚያነሳሳ ምክንያት አለመኖሩ፡- ሙስሊሞች (ሶሓቦች ረዲየላሁ ዐንሁም) በነቢዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘመን፡ በሰላምና በመልካም ሁኔታ ላይ ነበሩ፡፡ ቁርኣንን በቃላቸው የሚያነቡ ብዙ ሶሓቦችም ነበሩ፡፡ በኸሊፋው አቡ-በክር ሲዲቅ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የኺላፋነት ዘመን እንደነበረው አይነት ፊትናም ይፈጠራል የሚል ስጋት አልነበረም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ መልክተኛው ራሳቸው በመሐከላቸው በሕይወት ስላሉ፡ ቁርኣንን ለመሰብሰብና በአንድ መጽሐፍ ለማድረግ የሚያነሳሳ ነገር አልተፈጠረም ነበር፡፡
2ኛ/ ቅዱስ ቁርኣን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰበሰበው፡ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሞት ሁለት አመት በኋላ፡ በአቡ በክር አስ-ሲዲቅ ረዲየላሁ ዐንሁ ዘመነ ንግሥና ጊዜ ነው፡፡ አቡ በክር አስ-ሲዲቅ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ኸሊፋ በነበረበት ጊዜ፡ ኢስላምን በመልክተኛው የሕይወት ዘመን የተቀበሉ የተወሰኑ የዐረብ ጎሳዎች፡ ከሳቸው ሞት በኋላ ወደነበሩበት ክህደት ተመለሱ፡፡ ዘካንም ለመክፈል ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ኸሊፋው አቡ በክርም (ረዲየላሁ ዐንሁ)፡ እነዚህን ሙርተዶች ለመዋጋት በኻሊድ ኢብኑል-ወሊድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የሚመራ ጦርን አዘጋጀ፡፡ ጦርነቱም የሀሰተኛው ነቢይ ነኝ ባይ ሙሰይለመቱል-ከዛብ ሕዝቦች መንደር የሚገኘው ‹‹የማማህ›› በተሰኘው ስፍራ ነበር፡፡ ይህም በሂጅራ አቆጣጠር በአሥራ ሁለተኛው አመት ነበር፡፡ ጦርነቱም እጅግ የተቀጣጠለና የተፋፋመ ነበር፡፡ በመጨረሻም ሀሰተኛው ነቢይ ሙሰይለማህ ተገደለ፡፡ ህዝቦቹም ተሸነፉ፡፡ ከነሱ ውስጥም ከሞት የተረፉት ኢስላምን ተቀበሉ፡፡ ከሙስሊሞቹ በኩል ከአምስት መቶ እስከ ሰባት መቶ የሚደርሱት ሰማእት (ሸሂድ) ሆነዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ሰባ ያህሉ ቁርኣንን በቃላቸው ያጠኑ ነበሩ፡፡
የነዚህ የሰባዎቹ ቁርኣን ሐፊዞችና ቁርራኦች መገደል በሁለተኛው ኸሊፋ ዑመር ኢብኑል-ኸጥጧብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ልብ ላይ ስጋትን አሳደረ፡፡ የሐፊዞቹ ሰማእት መሆን፡ የተወሰነ የቁርኣን ክፍል በዚያው አብሮ ሊጠፋ ይችላል በሚል ስጋት፡ ወደ ኸሊፋው አቡ በክር (ረዲየላሁ ዐንሁ) ዘንድ በመምጣት፡ ቁርኣን በአንድ መጽሐፍ መልክ እንዲሰበሰብ ሀሳብ አቀረበ፡፡ ሙሉ ዘገባውን ከሶሒሕ አል-ቡኻሪይ ላይ እንዲህ ቀርቧል፡-
ዘይድ ኢብኑ-ሣቢት (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “አቡ በክር ሲድዲቅ (ረዲየላሁ ዐንሁ) በየማማህ ሰማእት ከሆኑት ሶሓቦች በኋላ ወደኔ እንዲህ የሚል መልክትን ላከ፡፡ (ዘይድ ኢብኑ-ሣቢት ሆይ!) ዑመር ኢብኑል-ኸጥጧብ እኔ ዘንድ መጣና፡- ‹‹በሶሓቦቹ ላይ ግድያው ተፋፍሟል፡፡ በሶሓቦቹ ላይ ከዚህ የበለጠ ግድያው እየበዛ ይሄድና በዚያውም በቃላቸው ያጠኑት ቁርኣን፡ አብዛኛው ክፍል አብሯቸው ሊጠፋ ይችላል የሚል ስጋት አለኝና፡ ቁርኣንን በአንድ መጽሐፍ እንዲሰበሰብ ብታዝበት መልካም ነው አለኝ፡፡ እኔም፡- እንዴት መልክተኛው ያልሰሩትን ሥራ ትሰራለህ? ስለው፡ ዑመርም፡- ወላሂ ይህ ሥራ መልካም ነው! መልክተኛውን መቃወም አይደለም! በማለት እኔን ከመወትወት አልተወገደም፡፡ በመጨረሻም አላህ ልቤን አሰፋልኝና ዑመር የተመከተውን ነገር እውነታነት እንደመለከት አደረገኝ፡፡ እናም ዘይድ ሆይ! ‹‹አንተ ገና ለጋ ወጣት ነህ፡፡ በዲንህም የማንጠራጠርህ ጥሩ አዕምሮ ያለህ ነህ፡፡ ለረሱላችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) በሕይወት እያሉ ወሕይን (ቁርኣንን) ከሚጽፉትም የቁርኣን ጸሐፍት አንዱ ነህ፡፡ ስለዚህ አሁንም ቁርኣንን በቃል ካጠኑት ሰዎች ጋር በማመሳከር፡ የተጻፉትን በመሰብሰብ በአንድ መጽሐፍ ሰብስበው›› አለኝ፡፡ በጌታዬ ይሁንብኝ! እኔ ግን ከተራራዎች መሐል አንዱን ከቦታው ንቀለው! ብለው ቢያዙኝ ኖሮ፡ ቁርኣንን ሰብስበው ብለው ካዘዙኝ ትእዛዝ የበለጠ አይከብድብኝም ነበር፡፡ ስለኾነም እንዲህ አልኳቸው፡- ‹‹እንዴት የአላህ መልክተኛ ሶለላሁ አለይሂ ወሰለም) ያልሰሩትን ነገር ትሠራላችሁ?›› አቡ በክርም (ረዲየላሁ ዐንሁ)፡- ‹‹ወላሂ! ይህ መልካም ሥራ ነው! ብሎ በመማል፡ በሥራው ላይ እንድሳተፍ ከመወትወት አልተወገደም፡፡ በመጨረሻም ለአቡ በክርና ለዑመር ልባቸውን ያሰፋው አላህ፡ እኔም ሥራው መልካም ኾኖ እንዲታየኝ ልቤን አሰፋልኝ፡፡ ከዚያም ቁርኣንን በመከታተል፡ በአማኞች ልቦና በቃል የሚያነቡትን ተጽፎ ከተቀመጡት ጋር እያመሳከርኩ ቁርኣንን ሰበሰብኩት” (ቡኻሪይ 4679, 4986, 6768)::
3ኛ/ ይህ ቅዱስ ቁርኣንን በአንድ መጽሐፍ የመሰብሰቡ ሥራ የተጠናቀቀው በአሥራ አምስት ወራት ውስጥ ነው፡፡ በሂጅራ አቆጣጠር በአሥራ ሁለተኛው አመት ጅማሬ ላይ ከየማማው ጦርነት በኋላ ተጀመረ፡፡ ለአሥራ አምስት ወራት የቆየ ኾነ፡፡ በአሥራ ሶስተኛው ዓመተ ሂጅራህ በስድስተኛው ወር ላይ ደግሞ (ከቁርኣኑ ተሰብስቦ መጠናቀቅ የተወሰነ ቆይታ በኋላ) አቡ በክር ሲዲቅ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ምድራዊ ቆይታቸውን በማጠናቀቅ ሞቱ ማለት ነው፡፡
በቀጣዩ ደግሞ፡- ቁርኣን በሶስተኛው ኸሊፋህ በዑሥማን ኢብኑ-ዐፍፋን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ዘመን! የሚለውን በአላህ ፈቃድ እንመለከተዋለን ኢንሻአላህ፡፡
ምንጭ፡- ዶክተር. ዓሊይ ኢብኑ ሱለይማን አል-ዑበይድ፡ جمع القرأن الكريم حفظا وكتابة
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


