ኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
2. “አል-ዋሒድ” (ፍጹም አንድና ብቸኛ)
ሀ. ትርጉም፡- “አል-ዋሒድ” የሚለው መለኮታዊ ስም ትርጉሙ አንድና ብቸኛ ማለት ነው፡፡ ጌታ አላህ በህልውናው (በዛቱ) የማይከፋፈል አንድ ጌታ በመሆኑ “አል-ዋሒድ” ይባላል፡፡ ጌታ አላህ ዩኒቨርሱን (አጽናፈ ዓለሙን) ሲፈጥር ያለ አጋርና ያለ አማካሪ ብቻውን ያዘጋጀ በመሆኑ “አል-ዋሒድ” ይባላል፡፡ ጌታ አላህ በባሕሪያቱና በስሞቹ አምሳያና ሞክሼ የሌለው ብቸኛ አምላክ በመሆኑ “አል-ዋሒድ” ይባላል፡፡ ጌታ አላህ ብቻውን የሚመለክና የሚሰገድለት እውነተኛ አምላክ በመሆኑ “አል-ዋሒድ” ተብሎ የሚጠራ ነው፡፡
ለ. አመጣጡ፡- “አል-ዋሒድ” የሚለው መለኮታዊ ስም በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ ሀያ አንድ ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-
“አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ (እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 163)፡፡
“እኔ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት፥ ወደኔ የሚወርድልኝ ቢጤያችሁ ሰው ብቻ፤ ነኝ፤ የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፤ መልካም ሥራን ይሥራ፤ በጌታውም መገዛት አንድንም አያጋራ፣ በላቸው።” (ሱረቱል ከህፍ 110)፡፡
“…እርሱ አሸናፊው አንዱ አላህ ነው።” (ሱረቱ-ዙመር 4)፡፡
ሐ. የምንወስደው ትምሕርት፡-
1. ሁለት አለመሆኑን፡- ፈጣሪ አምላካችን አላህ ፍጹም አንድ መሆኑ ሁለት ላለመሆኑ ሌላ መረጃ ነው፡፡ ሁለት አምላክ (የብርሐንና የጨለማ ፈጣሪ የሆኑ) አሉ ብለው የሚያምኑ ሰዎች (መጁሳዎች) የተሳሳቱ እንደሆኑ መረዳት ይቻላል፡-
“አላህ አለ፦ ሁለት አማልክትን አትያዙ፤ እርሱ አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ እኔንም ብቻ ፍሩ።” (ሱረቱ-ነሕል 51)፡፡
2. ሶስት አለመሆኑን፡- ጌታችን አላህ “አል-ዋሒድ” ተብሎ መገለጹ ሶስት ላለመሆኑ መረጃ ነው፡፡ አላህን በአንድነቱና በሶስትነቱ መግለጽ ፍጹም የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ በአንድነት ውስጥ ልይዩ ሶስትነት አልለ ብሎ ያስተማረ አንድም ነቢይ የለም፡፡ አንድ ከሶስት ያንሳል፡ ሶስትም ከአንድ ይበዛል፡፡ አንድ ሶስት መሆን አይችልም፤ ሶስትም አንድ ሊሆን አይችልም፡-
“እላንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፤ በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ፤ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ፣ የአላህ መልክተኛ፣ ወደ መርየም የጣላት (የሁን) ቃሉም ከርሱ የሆነ መንፈስም ብቻ ነው፤ በአላህና በመልክተኞቹም እመኑ (አማልክት) ሦስት ናቸው አትበሉም፤ ተከልከሉ ለናንተ የተሻለ ይሆናልና፤ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው። ለርሱ ልጅ ያለው ከመሆን የጠራ ነው። በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ የርሱ ነው። መመኪያም በአላህ በቃ።” (ሱረቱ-ኒሳእ 171)፡፡
“እነዚያ አላህ የሦስት ሦስተኛ ነው (ከሶስቱ አንዱ እሱ ነው) ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ ከአምላክም አንድ አምላክ እንጅ ሌላ የለም፤ ከሚሉትም ነገር ባይከለከሉ፣ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል።” (ሱረቱል ማኢዳህ 73)፡፡
3. ከሶስት በላይ አለመሆኑን፡- አምላካችን አላህ “አል-ዋሒድ” በመሆኑ፡ ከአንድ በላይ ብዙ አማልክት የሚያመልኩ ሰዎች የተሳሳቱና ጥመት ላይ ያሉ መሆናቸውን እንረዳለን፡-
“የእስር ቤት ጓደኞቼ ሆይ! የተለያዩ አምላኮች ይሻላሉን ወይንስ አሸናፊው አንዱ አላህ?” (ሱረቱ ዩሱፍ 39)፡፡
“«በምስክርነት ከነገሩ ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ማነው» በላቸው፡፡ (ሌላ መልስ የለምና) «አላህ ነው፡፡ በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ ነው፡፡ ይህም ቁርኣን እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ በርሱ ላስፈራራበት ወደኔ ተወረደ፡፡ ከአላህ ጋር ሌሎች አማልክት መኖራቸውን እናንተ ትመሰክራላችሁን» በላቸው፡፡ «እኔ አልመሰክርም» በላቸው፡፡ «እርሱ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ እኔም ከምታጋሩት ነገር ንጹሕ ነኝ» በላቸው፡፡” (ሱረቱል አንዓም 19)፡፡
4. ለሳቸው የወረደ ወሕይ መሆኑን፡- ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) ይወርድ የነበረው ወሕይ (መለኮታዊ ራእይ) አምላክ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው የሚለው ነበር ማለት ነው፡-
“እኔ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት፥ ወደኔ የሚወርድልኝ ቢጤያችሁ ሰው ብቻ፤ ነኝ፤ የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፤ መልካም ሥራን ይሥራ፤ በጌታውም መገዛት አንድንም አያጋራ፣ በላቸው።” (ሱረቱል ከህፍ 110)፡፡
“(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም። ያ ወደኔ የሚወረደው፣ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ነው፤ ታዲያ እናንተ ፍጹም ታዛዦች ናችሁን? በላቸው።” (ሱረቱል አንቢያእ 107-108)፡፡
“(እንዲህ) በላቸው፦ እኔ መሰላችሁ ሰው ብቻ ነኝ፤ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ወደርሱም ቀጥ በሉ፤ ምሕረትንም ለምኑት ማለት፣ ወደኔ ይወርድልኛል። ለአጋሪዎቹም ወዮላቸው።” (ሱረቱ ፉሲለት 6)፡፡
5. ቁርኣን የወረደበት አንዱ ዓላማ መሆኑን፡- ቅዱስ ቁርኣን አንዱ የወረደበት ዓላማ ይህንኑ የአምላክን አንድነት ለማስተማር ነው፡-
“ይህ (ቁርአን) ለሰዎች ገላጭ ነው፤ (ሊመከሩበት) በርሱም ሊስፈራሩበት እርሱም አንድ አምላክ ብቻ መሆኑን ሊያውቁበት የአእምሮ ባለቤቶችም ሊገሠጹበት (የተወረደ) ነው።” (ሱረቱ ኢብራሂም 52)፡፡
“የመጽሐፉን ባለቤቶችም በዚያች እርሷ መልካም በሆነችው ክርክር እንጂ አትከራከሩ፤ ከነሱ ነዚያን የበደሉትን ሲቀር በሉም ፦ በዚያ ወደኛ በተወረደው፣ ወደናንተም በተወረደው አመንን፤ አምላካችንም አምላካችሁም አንድ ነው፤ እኛም ለርሱ ታዛዦች ነን።” (ሱረቱል ዐንከቡት 46)፡፡
6. ሰዎች በአንዱ አላህ ማመን እንደሚገባቸው፡- የጣኦት አምልኮን ትተው በአላህ አንድነት ሰዎች እስካላመኑ ድረስ ከክህደት ዓለም ሊላቀቁ አይችሉም፡፡
“በኢብራሂምና በነዚያ ከርሱ ጋር በነበሩት (ምእመናን) መካከል መከተል አለቻችሁ። ለሕዝቦቻቸው፦ እኛ ከናንተ ከአላህ ሌላ ከምትግገዙትም ንጹሖች ነን በናንተ ካድን፤ በላህ አንድ ብቻ ሲሆን እስከምታምኑ ድረስ በኛና በናንተ መካከል ጠብና ጥላቻ ዘወትር ተገለጸ፤ ባሉ ጊዜ( መልካም መከተል አለቻችሁ)…” (ሱረቱል ሙምተሒናህ 4)፡፡
7. ከኩፍር ጋር ኅብረት እንደሌለው፡- ካፊሮችና ሙሽሪኮች (በአላህ የሚያጋሩ) የአላህ ፍጹማዊ አንድነት ሲወሳ፡ እሱ ብቻውን መመለክ እንዳለበት ሲነገር አይስማማቸውም፡፡ ውስጣቸውን ይረብሸዋል፡፡
“አንድ አላህን ብቻውን እንድንገዛ አባቶቻችንም ይግገዙት የነበረውን (አማልክት) እንድንተው መጣህብን? ከውነተኞች ከሆንክ የምታስፈራራብንን (ቅጣት) አምጣብን አሉ።” (ሱረቱል አዕራፍ 70)፡፡
“ቁርአንንም ባነበብክ ጊዜ ባንተና በነዚያ በመጨረሻይቱ ዓለም በማያምኑት ሰዎች መካከል የሚሸሽግን ግርዶሽ አድርገናል። እንዳያውቁትም በልቦቻቸውም ውስጥ ድንቁርናን አደረግን፤ ጌታህንም ብቻውን ሆኖ በቁርአን ባወሳኸው ጊዜ የሚሸሹሆነው በጀርቦቻቸው ላይ ይዞራሉ።” (ሱረቱል ኢስራእ 46)፡፡
“በል፦ እርሱ አላህ አንድ ነው። አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው። አልወለደም፤ አልተወለደምም። ለርሱም አንድም ብጤ የለውም።” (ሱረቱል ኢኽላስ 1-4)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


