ኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
” إِنَّهُ لَقَوْلُ رَسُولٍ كَرِيمٍ * وَمَا هُوَ بِقَوْلِ شَاعِرٍ قَلِيلًا مَا تُؤْمِنُونَ * وَلَا بِقَوْلِ كَاهِنٍ قَلِيلًا مَا تَذَكَّرُونَ * تَنْزِيلٌ مِنْ رَبِّ الْعَالَمِينَ ” سورة الحاقة 43-40
“እርሱ (ቁርኣን) የተከበረ መልክተኛ ቃል ነው፡፡ እርሱም የባለቅኔ ቃል (ግጥም) አይደለም ጥቂትን ብቻ ታምናላችሁ። የጠንቋይም ቃል አይደለም ጥቂቱን ብቻ ታስታውሳላችሁ። ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው” (ሱረቱል-ሓቃህ 40-43)፡፡
” إِنَّهُ لَقَوْلُ رَسُولٍ كَرِيمٍ * ذِي قُوَّةٍ عِنْدَ ذِي الْعَرْشِ مَكِينٍ * مُطَاعٍ ثَمَّ أَمِينٍ ” سورة التكوير 21-19
“እርሱ (ቁርኣን) የክቡር መልክተኛ ቃል ነው፡፡ የኃይል ባለቤት፡ በዙፋኑ ባለቤት ዘንድ ባለሟል የሆነ፡፡ በዚያ ስፍራ ትዕዛዙ ተሰሚ ታማኝ የሆነ (መልክተኛ ቃል) ነው፡፡” (ሱረቱ-ተክዊር 19-21)፡፡
ከነዚህ ሁለት የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች በመነሳት አንዳንድ ክርስቲያን ወገኖች ቁርኣን የጂብሪል (ዐለይሂ ሰላም) ቃል እንጂ የአላህ አይደለም ይሉናል፡፡ እኛም ለቀረቡት የቅዱስ ቁርኣን ጥቅሶች ምላሻችንን ከመስጠታችን በፊት አንድ ጥያቄ እናቅርብላቸው፡፡ እሱም፡- ባቀረባችሁት ሁለት የቁርኣን ጥቅሶች መሰረት፡ ቅዱስ ቁርኣን የጂብሪል ቃል ነው ብላችሁ ስትሞግቱን፡ እናንተ የጂብሪል ቃል መሆኑን አምናችሁ ተቀብላችሁ ነውን? ወይስ እንዲሁ ሳታምኑበት ለሙግት ብቻ?
አዎ የጂብሪል ቃል ነው! ብለን እናምናለን ካላችሁ፡ እንግዲያውስ መልአኩ ጂብሪል አይዋሽምና በቃሉ ውስጥ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ መልክተኛና የነቢያት መደምደሚያ መሆናቸውን መስክሯል (ሱረቱል-አሕዛብ 40)፡፡ ስለዚህ እናንተም መልአኩ ባለው መሰረት ለምን በሳቸው ነቢይነት አታምኑም?
አይ እኛ በነቢዩ ሙሐመድ ነቢይነት አናምንም፡፡ ቁርኣንም የጂብሪል ቃል ነው ብለን አንቀበልም! ከሆነ ምላሻችሁ፡ እንግዲያውስ ከቁርኣን ውስጥ ጥቅስ አውጥቶ ማስረጃ መጠቀሙ ለምን አስፈለገ? እኛ ሙስሊሞች ከመጽሐፋችሁ ውስጥ ጥቅስ መዝዘን ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን የሚያመላክት ጥቅስ ብናሳያችሁ ፡ ነቢይ መሆኑን ስላመንን ነው እንጂ ለጭቅጭቅ አይደለም፡፡ ታዲያ የናንተን ከቁርኣን ጥቅስ መምዘዝ ምን እንበለው? እንዲሁ ግራ ለማጋባት? ወይስ የናንተ መጽሐፍ ላይ ጥያቄ እንዳናበዛና በራሳችን እምነት ላይ ለሚነሳው ጥያቄ ብቻ መልስ መስጠቱ ላይ እንድንጠመድ? ለማንኛውም ጉዳዩን ለህሊና እንተወውና ወደ ትክክለኛ ፍቺውና ማብራሪያ እንግባ፡-
ቅዱስ ቁርኣን ከሱረቱል-ፋቲሓ እስከ ሱረቱ-ናስ ያለው 114ቱም ሱራ የአላህ ቃል ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩት ቃላት በጠቅላላ የአላህ ናቸው፡፡ ቃሉም መልእክቱም የራሱ ነው፡፡ የመላእክት፣ የነቢያትና የተራ ምእመኖች ሀሳብ ጣልቃ አልገባበትም፡ አይገባበትምም፡፡ ሁሌም ቃሉን ስናስተምርም ሆነ ስንማር የምንሰማው ‹አላህ እንዲህ አለ› የሚል እንጂ፡ ‹እንትና እንዲህ አለ› ሲባል አይደለም፡፡ ከላይ የቀረቡትም ሁለት የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች ከዚሁ ሀሳብ ጋር የሚስማሙ እንጂ የሚጣረሱ አይደሉም፡፡ ዝርዝር ሃሳባቸውንም በኋላ ላይ እንመለስበታለን፡፡ ቅዱስ ቁርኣን ከአላህ ዘንድ የመጣ የራሱ የአላህ ቃል መሆኑን የሚያመላክቱ ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ጥቂቱን እንመልከተው፡-
1. በቀጥታ የአላህ ንግግር መባሉ፡-
አንዱና ዋነኛው ማስረጃችን ነው፡፡ በቀጥታና ግልጽ በሆነ መልኩ ቁርኣን የአላህ ቃል እንደሆነ እራሱ ቁርኣን ይነግረናል፡፡ እንዲህ ይላል፡-
” وَإِنْ أَحَدٌ مِنَ الْمُشْرِكِينَ اسْتَجَارَكَ فَأَجِرْهُ حَتَّى يَسْمَعَ كَلَامَ اللَّهِ ثُمَّ أَبْلِغْهُ مَأْمَنَهُ ذَلِكَ بِأَنَّهُمْ قَوْمٌ لَا يَعْلَمُونَ ” سورة التوبة 6
“ከአጋሪዎችም አንዱ ጥገኝነትን ቢጠይቅ የአላህን ቃል ይሰማ ዘንድ አስጠጋው፤ ከዚያም ወደ መጠበቂያዉ ስፍራ አድርሰው፤ ይህ እነሱ የማያዉቁ ሕዝቦች በመሆናቸው ነው።” (ሱረቱ-ተውባህ 6)፡፡
ጥገኝነትን ለጠየቀ አንድ ሙሽሪክ (በአላህ የሚያጋራ) ከለላን ስጠው ብሎ ጌታችን አላህ አዘዘና፡ እግረ መንገድም ‹የአላህን ቃል አሰማው› በማለት፡ የቁርኣን ቃላት የአላህ ንግግሮች እንደሆኑ መሰከረ ማለት ነው፡፡
2. ከሱ ዘንድ መባሉ፡-
በብዙ የቁርኣን ክፍሎች ላይ ቁርኣን ለነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የተሰጠው ከጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) ሳይሆን ከአላህ ዘንድ መሆኑን በመግለጽ፡ የቃሉ ባለቤት አላህ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ የጂብሪል ቃል ቢሆን ኖሮ ‹ከሱ ዘንድ› መሆኑን የሚያመላክት አንድ ጥቅስ እንኳ ባገኘን ነበር፡፡ ግን የለም፡ ሊኖርም አይችልም፡፡
” وَإِنَّكَ لَتُلَقَّى الْقُرْآنَ مِنْ لَدُنْ حَكِيمٍ عَلِيمٍ ” سورة النمل 6
“አንተም ቁርኣንን ጥበበኛና ዐዋቂ ከሆነው (ጌታህ) ዘንድ በእርግጥ ትሠጣለህ።” (ሱረቱ-ነምል 6)፡፡
“እንደዚሁ በእርግጥ ካለፉት ወሬዎች ባንተ ላይ እንተርካለን፤ ከኛም ዘንድ ቁርኣንን በእርግጥ ሰጠንህ።” (ሱረቱ ጣሀ 99)፡፡
3. የመጽሐፉ መወረድ ከአላህ ነው መባሉ፡-
ቅዱስ ቁርኣን ከአላህ ዘንድ ወደ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ልብ የተወረደ ነው በማለት ይገልጻል፡-
” الم • تَنْزِيلُ الْكِتَابِ لَا رَيْبَ فِيهِ مِنْ رَبِّ الْعَالَمِينَ ” سورة السجدة 2-1
“አ. ለ. መ. ( አሊፍ ላም ሚም)። የመጽሐፉ መወረድ ጥርጥር የለበትም፤ ከዓለማት ጌታ ነው።” (ሱረቱ-ሰጅዳህ 1-2)፡፡
“የመጽሐፉ መወረድ፣ አሸናፊውና ጥበበኛ ከሆነው አላህ ነው።” (ሱረቱ-ዙመር 1)፡፡
4. አምሳያውን ማንም ሊያመጣው አይችልም መባሉ፡-
ፍጹም አምሳያ የሌለው ነገር ቢኖር ጌታችንና አምላካችን አላህ ብቻ ነው (ሱረቱ-ሹራ 11)፡፡ ቅዱስ ቁርኣንም ከሱ ዘንድ የሆነ መለኮታዊ ቃል እንጂ ፍጥረታዊ ቃል ባለመሆኑ ማንም አምሳያውን ሊያመጣው አይችልም ይለናል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
“ወይንስ ቀጠፈው ይላሉን አይደለም በእውነቱ አያምኑም፡፡ እውነተኞችም ቢሆኑ መሰሉ የሆነን ንግግር ያምጡ” (ሱረቱ-ጡር 33-43)፡፡
“ይልቁንም (ቁርኣንን) ቀጣጠፈው ይላሉን? ፡- እውነተኞች እንደሆናችሁ ብጤው የሆኑን አስር የተቀጣጠፉ ሱራዎች አምጡ፡፡ ከአላህም ሌላ የቻላችሁትን (ረዳት) ጥሩ በላቸው” (ሱረቱ ሁድ 13)፡፡
“በእውነትም (ሙሐመድ) ቀጣጠፈው ይላሉን? ይህ ከሆነ መሰሉን (አንዲት) ሱራ አምጡ ከአላህም ሌላ የቻላችሁትን ሁሉ (ረዳት) ጥሩ እውነተኞች እንደሆናችሁም (ተጋግዛችሁ አምጡ) በላቸው” (ሱረቱ ዩኑስ 38)፡፡
” وَإِنْ كُنْتُمْ فِي رَيْبٍ مِمَّا نَزَّلْنَا عَلَى عَبْدِنَا فَأْتُوا بِسُورَةٍ مِنْ مِثْلِهِ وَادْعُوا شُهَدَاءَكُمْ مِنْ دُونِ اللَّهِ إِنْ كُنْتُمْ صَادِقِينَ ” سورة البقرة 23
“በባሪያችንም ላይ ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆኑ ከብጤው አንዲትን ምእራፍ አምጡ እውነተኞችም እንደሆናችሁ ከአላህ ሌላ መስካሪዎቻችሁን ጥሩ” (ሱረቱል-በቀራህ 23)፡፡
ይህም ሳይሆንላቸው ሲቀር አላህ ግን፡- ጋኔኖችንም ጨምራችሁ ብትተባበሩ እስከ ትንሳኤ ቀን (የውሙል ቂያም) ድረስ አምሳያውን ልታመጡ አትችሉም በማለት ቁርጡን ነገራቸው፡፡
“ሰዎችም ጋኔኖችም የዚህን ቁርኣን ቢጤ በማምጣት ላይ ቢሰባሰቡ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳት ቢሆንም እንኳ ብጤውን አያመጡም በላቸው” (ሱረቱል-ኢስራእ 88)፡፡
በተለይ በሱረቱ ሁድ ላይ “ከአላህም ሌላ የቻላችሁትን (ረዳት) ጥሩ በላቸው” የሚለው :ቁርኣን የጂብሪል ቃል ላለመሆኑ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ “ከአላህ ሌላ ያለን ሁሉ ለረዳትነት ጥሩ” ከተባሉ፡ መልአኩ ጂብሪልም ከፈለገ ያግዛችሁ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እሱ አላህ አይደለም፡፡ እንግዲያውስ ጂብሪል እራሱ ቢተባበራቸው እንኳ አምሳያውን ማምጣት ካልቻለ፡ እንዴት ሁኖ ነው ቁርኣን የሱ ቃል የሚሆነው? የራሱን ቃል አምሳያ ማምጣትስ ይሳነዋልን? አላህ የሚገነዘብ ልብ ይስጠን፡፡
5. የንግግር ዘይቤው፡-
በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ የመጀመሪያ መደብ መጠሪያ ‹እኔነት› በአምልኮ አንቀጾች ላይ በስፋት ይታያል፡፡ ለምሳሌ፡- እኔ አምላካችሁ ነኝ፣ እኔን ብቻ ፍሩኝ፣ እኔን ብቻ ተገዙኝ፣ ከኔ ሌላ አምላክ የለም….፡፡ ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው፡ እነዚህን ንግግሮች መልአኩ ጂብሪል ደፍሮ ይናገራል ብሎ ይጠረጥራልን? ከአላህ በስተቀር ማን እንደዚህ ብሎ ይናገራል? ቀጣዮቹን ለምሳሌ እንመልከታቸው፡-
“…ዛሬ እነዚያ የካዱት ከሃይማኖታችሁ ተስፋ ቆረጡ ስለዚህ አትፍሩዋቸው ፍሩኝም…” (ሱረቱል-ማኢዳህ 3)፡፡
“ጌታችሁም አለ፡- ለምኑኝ እቀበላችኋለሁና…” (ሱረቱ ጋፊር 60)፡፡
“ከአንተ በፊትም እነሆ ከኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢሆን እንጂ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡” (ሱረቱል-አንቢያእ 25)፡፡
“ይህች (ህግጋት) አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት እኔም ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ” (ሱረቱል-አንቢያእ 92)፡፡
“እናንተ ያመናችሁ ባሮቼ ሆይ ምድሬ በአርግጥ ሰፊ ናት (ብትቸገሩ ተሰደዱ) እኔንም ብቻ ተገዙኝ” (ሱረቱል ዐንከቡት 56)፡፡
ፍሩኝ፣ ለምኑኝ፣ ከኔ ሌላ አምላክ የለም፣ ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ ብሎ የሚናገረው ጂብሪል ነው ብሎ ማሰብ የጤና ነውን? ከመላእክት መካከል ይህን ደፍሮ የሚናገር ቢኖር ኖሮ የሚገጥመው ምን እንደሚሆን ጌታችን እንዲህ ይገልጸዋል፡-
“ከነሱም እኔ ከርሱ ሌላ አምላክ ነኝ የሚል ያንን ገሀነምን እንመነዳዋለን፤ እንደዚሁ በዳዮችን እንመነዳለን።” (ሱረቱል አንቢያእ 29)፡፡
6. “በል!” የሚለው ትእዛዝ በውስጡ መገኘቱ፡-
መልእክተኛ የሆነ ሰው መልእክቱን በአግባቡ ሳይሸራረፍ ወደተላከበት ቦታ ያደርሳል እንጂ፡ ያንኑ የታዘዘውን ነገር ቃል በቃል ያስተላልፋል አይባልም፡፡ ለምሳሌ፡- እናትህ አንተን፡- ወደ ጎረቤት ሂድና ወይዘሮ አዒሻን ኑ ቡና ጠጡ! ብለህ በጆሮአቸው ቀስ ብለህ ንገራቸው! ብትባል፡ ሄደህ ኑ ቡና ጠጡ ተብለዋል ብለህ ትነግራቸዋለህ እንጂ፡ ወይዘሮ አዒሻ! ቀስ ብለው በጆሮዎት ቡና ጠጡ ተብለዋል ትላለህ? አትልም፡፡ ቀስ ብለህ በጆሮአቸው የሚለው ላንተ የተሰጠ ትእዛዝ ነው፡፡ ቡና ጠጡ የሚለው ደግሞ ለሳቸው እንዲደርሳቸው የተፈለገ መልክት ነው፡፡ ቁም ነገሩ መልክቱን ማድረሱ ላይ ስለሆነ፡ አንተ ከፈለግህ፡ ኑ ቡና ተጠርተዋል ወይንም ቡና ፈልቷል ኑ ጠጡ ልትል ትችላለህ፡፡ የታዘዝከው መልክት እንድታደርስ እንጂ ቃሉን ከነፊደላቱ እንድትደግም አይደለም፡፡ ወደ ቅዱስ ቁርኣን ግን ስንመጣ ከዚህ የተለየ ነገር ነው የምናገኘው፡፡ ቁርኣን ከላይ እንደወረደ ፊደል ሳይጨመርበትና ሳይቀነስበት የተጻፈ መለኮታዊ ቃል ነው፡፡ ያንን ከሚገልጹት ውስጥ አንዱ “በል” የሚሉት መለኮታዊ ትእዛዛት በውስጡ መገኘታቸው ነው፡፡ ሱረቱል-ኢኽላስን ብቻ ለናሙና እንመልከት፡-
“በል እርሱ አላህ አንድ ነው አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው አልወለደም አልተወለደምም ለርሱም አንድም ብጤ የለውም” (ሱረቱል ኢኸላስ 1-4)፡፡
ይህ ሱራ የወረደበት ምክንያት፡- ዐረብ ጣኦታውያን (ሙሽሪኮች) ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ዘንድ በመምጣት፡- አንተ የምትገዛውን ጌታ ባሕሪ ግለጽልን በማለት በመጠየቃቸው ነው፡፡ እሳቸውም ምላሽን ይሰጡ ዘንድ ከአላህ ዘንድ ሱረቱል ኢኽላስ በመውረድ እንዲህ ብለህ ንገራቸው የሚል መልስ ተሰጣቸው፡፡
በሱራው የመጀመሪያ አንቀጽ ላይ የመጀመሪያው ኃይለ ቃል ‹ቁል› (በል) የሚለው ነው፡፡ ከአላህ ዘንድ ቃሉ ወደሳቸው ሲመጣ ትእዛዝ ሆኖ መምጣቱን ያሳያል፡፡ የሚገርመው ግን እሳቸውም ለነዚያ ጠያቂዎች መልሱን ሲያነቡላቸው ‹በል› የሚለውን ቃል አስቀርተው ሌላውን ሳይሆን: ‹በል› የሚለውንም ጭምር ነው ያነበቡላቸው፡፡ እሳቸው ‹ቁል› (በል) የሚለውን ሲያነቡ ማንን እያዘዙ ነበር? ማንንም፡፡ ነገር ግን ቃሉ ከላይ እንደወረደ ሳይጨመርበትና ሳይቀነስበት እንዲሁም በሌላ ቃል ሳይተካ እንዳለ መነበብና መጻፍ ስለነበረበት እሳቸውም ይህንኑ አደረጉ፡፡ የሳቸው ተከታይ የሆን እኛም ዛሬ ሱረቱል ኢኽላስን ስናነብ ‹ቁል› እያልን እናነባለን፡፡ እያዘዝን ግን አይደለም፡፡ ጌታችን አላህ ያዘዘበትን መለኮታዊ ቃሉን በማንበብ እኛም እየደገምነው እንጂ፡፡
ታዲያ ይህ አንቀጽ ብቻ ቁርኣን የአላህ ቃል ለመሆኑ በቂ አይሆንም ነበርን?
እነዚህ ስድስት መንገዶች ከብዙ በጥቂቱ አንባቢን ላለመሰልቸት የቀረቡ መረጃዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ቁዱስ ቁርኣን የአምላካችን የአላህ ቃል እንጂ የጂብሪል አይደለም፡፡ እውነታው ይሄ ከሆነ፡ በጽሑፋችን መግቢያ ላይ ያቀረብናቸው ሁለት የቁርኣን ጥቅሶችን እንዴት ነው የምንፈታቸው? ወደሚለው እንግባ፡-
1ኛ. ሁለቱ የቅዱስ ቁርኣን ጥቅሶች የሚናገሩት ስለ አንድ አካል ‹ጂብሪል› ሳይሆን፡ ስለ ሁለት አካል ‹ጂብሪልና ነቢዩ ሙሐመድ› ነው፡፡ የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ ‹የተከበረ መልክተኛ› የተባሉት ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንጂ መልአኩ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) አይደለም፡፡ በውስጡ ‹‹እርሱም የባለቅኔ ቃል (ግጥም) አይደለም›› የሚል ቃል አለ፡፡ ባለ ቅኔ ተብለው በጣኦታዊያን የተሰደቡት እሳቸው እንጂ ጂብሪል አይደለምና፡፡ እንደገናም ‹‹የጠንቋይም ቃል አይደለም ›› ይላል፡፡ ማነው እብድና ጠንቋይ እየተባለ በህዝቦቹ ሲሰደብ የነበረው? መልአኩ ጂብሪል? በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡ ደግሞስ እሱን የት አግኝተውት? በመሆኑም ‹የተከበረ መልክተኛ› የሚለው ለሳቸው መሆኑን ልብ ይበሉ፡፡
ሁለተኛው አንቀጽ ደግሞ የሚናገረው ስለ ጂብሪል ነው፡፡ በውስጡ ‹የኃይል ባለቤት› የሚል ቃል አለ፡፡ በዚህ ባህሪ የሚገለጸው መልአኩ ጂብሪል ነው፡፡ (ሱረቱ-ነጅም 5-6)፡፡ እንዲሁም ‹በዚያ ስፍራ ትእዛዙ ተሰሚ› መባሉ ጂብሪል መሆኑን ያሳየናል፡፡ በመላእክት ዘንድ ቃሉ ተሰሚና አለቃቸው የሆነው መልአክ ጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) ነውና፡፡
በሁለቱም አንቀጾች ላይ ‹ክቡር መልክተኛ› ተብሎ የተጠቀሰው የተለያየ አካል መሆኑ ቁርኣንን ወደ አንዱ አስጠግተን «የእንትና ቃል ነው» እንዳንል ያግደናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም የጂብሪል ቃል ነው! የሚሉ ሰዎች ሃሳብ ውድቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡
2ኛ. እንግዲያውስ ‹ክቡር መልክተኛ› የሚለው ለነቢዩ ሙሐመድና ለመልአኩ ጂብሪል ከሆነ፡ ቁርኣኑን ወደነሱ በማስጠጋት ‹የክቡር መልከተኛ ቃል ነው› ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ አዎ መነሳትም አለበት፡፡ መልሱም ቀላል በመሆኑ፡፡ እሱም፡-
ሀ. ቁርኣንን ወደ ጂብሪል በማስጠጋት ‹የክቡር መልክተኛ ቃል ነው› ብሎ ሲናገር፡ ጂብሪል ከራሱ ያፈለቀው፡ የራሱ ሀሳብና ቃል ነው ለማለት ሳይሆን፡ ከአላህ ዘንድ መልእክቱን እንዲያደርስ የተመረጠ መልክተኛ በመሆኑና መልክቱንም በታማኝነት ሳይጨምርና ሳያጎድል በማድረሱ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው እዛው አንቀጽ ላይ ጥቅሱ ስለ ጂብሪል ሲናገር ፡- ‹‹ታማኝ የሆነ›› ይለዋል፡፡ ጂብሪል ‹ታማኝ ነው› የሚለው ቃል ትርጉም የሚኖረው፡ ከሌላ አካል ዘንድ መልእክት ተሰጥቶት ያንን የተሰጠውን መልእክት በአግባቡ ሲያደርስ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ቁርኣን የራሱ ቃል ከነበረማ፡ የራሱን ቃል ማድረሱ ነው ታማኝ የሚያስብለው? እንዴትስ ሊሆን ይችላል? ደግሞም በሌሎች የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች ላይ ጂብሪል ታማኝ መልክተኛ ሆኖ ቁርኣኑን አወረደው መባሉ የጉዳዩን እውነተኝነት ይበልጥ ያጎላዋል፡፡ ለምሳሌ፡-
“እርሱም (ቁርኣን) በእርግጥ ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡ እርሱን ታማኙ መንፈስ (ጂብሪል) አወረደው” (ሱረቱ-ሹዐራእ 192-193)::
“ለጂብሪል (ለገብርኤል) ጠላት የኾነ ሰው (በቁጭት ይሙት) በላቸው፡፡ እርሱ (ቁርኣኑን) ከበፊቱ ለነበሩት (መጻሕፍት) አረጋጋጭ ለምእመናን መሪና ብስራት ሲኾን በአላህ ፈቃድ በልብህ ላይ አውርዶታልና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 97)፡፡
“እነዚያን ያመኑትን ለማረጋጋት ሙስሊሞቹንም ለመምራትና ለማብሰር (ቁርአንን)፣ ቅዱሱ መንፈስ (ጂብሪል) እውነተኛ ሲሆን ከጌታህ አወረደው በላቸው።” (ሱረቱ-ነሕል 102)፡፡
ለ. ቁርኣንን ወደ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) በማስጠጋት ‹የተከበረ መልክተኛ ቃል ነው› በማለት ሲናገር ደግሞ ትርጉሙም፡- እሳቸው ቁርኣን በመልአኩ ጂብሪል አማካኝት ከጌታቸው ተቀብለው በታማኝነት ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ፡ አላህ ያላለውን ብሏል ሳይሉ ለህዝባቸው በማስተላለፋቸው ነው፡፡ በዛው ሱራ ላይ ቀጥሎ ጌታችን እንዲህ ብሎ መናገሩ ማጠናከሪያ ይሆነናል፡-
“በኛ ላይም ከፊልን ቃላት (ያላልነውን) በቀጠፈ ኖሮ፤በኅይል በያዝነው ነበር። ከዚያም ከርሱ የልቡን ስር (የተንጠለጠለበትን ጂማት) በቆረጥን ነበር።” (ሱረቱል-ሓቃህ 44-46)፡፡
በዚህ አንቀጽ መሰረት እሳቸውም ቁርኣኑን ከጌታቸው እንደተቀበሉ ለህዝባቸው በታማኝነት ማድረሳቸውን መረዳት እንችላለን፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ከላይ በተጠቀሰው አንቀጽ ውስጥ የተነገረው የቅጣት ቃል በተፈጸመ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ የተላከው መልክተኛ ታማኝ ነበርና (ሶላዋቱላሂ ወሰላሙሁ አለይህ)፡፡
በዚህ መልኩ ነው ሁለቱን መልክተኞች (የሰውና የመልአክ) ቁርኣንን ወደነሱ በማስጠጋት ‹የክቡር መልክተኛ ቃል› ያለው እንጂ፡ እነሱ ያፈለቁት የራሳቸው ሀሳብና ድርሰት የሆነ ለማለት አይደለም፡፡
3ኛ. በሁለቱም አንቀጾች ላይ ‹ረሱል› (መልክተኛ) የሚል ቃል አለ፡፡ ይህ ደግሞ ቁርኣኑ የነሱ ቃል ላለመሆኑ ሌላ ማስረጃችን ነው፡፡ እንዴት የሚሉም ከሆነ፡-
ረሱል (መልክተኛ) የሚለው ቃል በውስጡ ሁለት ነገሮችን ያቀፈ ነው፡፡ እነሱም፡- ላኪና የተላከው መልእክት!፡፡
ከመልአኩ ጂብሪል እንነሳና እሱ መልክተኛ ነው ካልን፡ ማን ላከው? ተብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ መልስ የሚሆነውም አላህ ስንል ነው፡፡ ምንድነው የተላከው? በማለት በድጋሚ ስንጠየቅ፡ ቁርኣን ብለን ከመለስን፡ እንግዲያውስ ቁርኣኑ የላኪው እንጂ የመልክተኛው ጂብሪል አይደለም ማለት ነዋ! ልንባል ነው፡፡ አዎ ቁርኣን የላኪው የአላህ ቃል እንጂ የተላኪው የጂብሪል አይደለም፡፡ ቃሉ የጂብሪል ከሆነ በራሱ ቃል ላይ እንዴት መልክተኛ ሊሆን ይችላል? የራሱን ሃሳብና መልክት ወደናንተ ይዞ በመምጣት፡ ተልኬ ነው የመጣሁት የሚል ሰው ገጥሟችኋልን?
ከነቢያችንም ብንነሳ፡ እሳቸው መልክተኛ ከሆኑ፡ የላካቸው አላህ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የተላኩት ደግሞ የተሰጣቸውን ቁርኣን ለሰዎች እንዲያደርሱ ነው፡፡ ስለዚህ ቁርኣን የአላህ ቃል እንጂ የጂብሪልም ሆነ የነቢዩ ሙሐመድ ቃል አይደለም፡፡
ጌታችን አላህ ሆይ! ከክህደትና ከሰባኪያኑም ፈተና ጠብቀን፣ በእውነተኛይቱ ሃይማኖት በኢስላም ላይ ጽናትን ስጠን፣ ፍጻሜችንንም በማሳመር ሙስሊም አድርገህ ግደለን፡፤ አላሁመ አሚን፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


